ብዙዎች እናቶች የተስተካከለና ችግር የሌለበት/ኖርማል የእርግዝና ወቅት ያሳልፋሉ። ሆኖም ግን በእርግዝናዎ ወቅት አንዳንዴ ሊታዩ የሚችሉ የማስጠንቀቂያ ምልክቶችን ማወቁ አስፈላጊ ነገር ነዉ፡፡ ምንም እንኳ የህክምና ባለሙያዎ የእርስዎን እርግዝና የሚመለከት አስፈላጊዉን ነገር የሚነግርዎ ቢሆንም ማንኛዉም በእርግዝና ወቅት ለሚመጣ ችግር መጠነኛ ተጋላጭ ናቸዉ የሚበሉትም እናቶች እንኳ ሳይቀር ስለአጠቃላይ በእርግዝና ወቅት ሊታዩ ለሚችሉ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ማወቅ ያስፈልጋቸዋል፡፡
በእርግዝናዎ ወቅት ከሚከተሉት ዉስጥ አንዱ እንኳ ካለዎ ባፋጣኝ የህክምና ባለሙያዎን ማነጋገር ያስፈልጋል፡፡ የህክምና ባለሙያዎን ማነጋገር ከዚህ የበለጠ ችግሮችን እንዴት ማወቅ እንደሚችሉ ይረዳዎታል፡፡ ችግሮችን/የማስጠንቀቂያ ምልክቶቹን ባዩበት ወቅት ወዲያዉ ሕክምና ያለማግኘትና መዘግየት ችግሩን የከፋ ሊያደርገዉ ስለሚችል ምልክቶቹን ባዩበት ወቅት ማማከር ተገቢ ይሆናል፡፡
በእርግዝና ወቅት ሊታዩ የሚችሉ የማስጠንቀቂያ/የአደጋ ምልክቶች ዉስጥ፡-
• ከብልት በኩል መድማት ካለ (Vaginal Bleeding)፡- ይህ ሁኔታ ሲከሰት ምክንያቱ የተለያየ ነገር ሊሆን ይችላል፡፡ ከነዚህ ዉስጥ ዉርጃ፣ የእንግዴ ልጅ ከማህፀን ግድግዳ ላይ መላቀቅ (placental abruption)፣ የእንግዴ ልጅ አቀማመጥ ችግር መኖር (placenta previa) እና ሌሎች እንደ ከሆርሞን ጋር የተገናኘ መድማት ወይም ፅንሱ ከማህፀን ግድግዳ ጋር በሚጣበቅበት ወቅት (Implantation bleeding) ሊሆን ይችላል፡፡
• የዳሌ ዉስጥ ወይም የሆድ ህመም/ቁርጠት መኖር፡- ይህ ዉርጃ፣ ከማህፀን በላይ እርግዝናና የእንግዴ ልጅ ከማህፀን ግድግዳ ላይ መላቀቅ ሲኖር የሚመጣ የህመም አይነት ሲሆን በተጨማሪም ዕጢዎች(ሲስት) ካሉ፣ የማህፀን እድገትና የጅማት ላይ ህመሞችም ይህ ሁኔታ እንዲከሰት ያደርጋሉ፡፡
• ተደጋጋሚ የሆነ/ የማያቋርጥ የጀርባ ላይ ህመም መከሰት፡- ይህ ዉርጃን፣ ያለጊዜዉ የሚከሰት ምጥ መምጣት ሊያመላክት የሚችል ሲሆን በተጨማሪም የኩላሊት/የፊኛ ኢንፌክሽን፣ ሲስት(ዕጢ) ሲከሰትና በኖርማል እርግዝና ወቅትም ሊኖር ይችላል፡፡
• ከብልትዎ የሚፈስ ፈሳሽ ካለዎ( Gush of Fluid from Vagina)፡- የእንሽርት ዉሃ ያለጊዜዉ መፍሰስ፣ ያለጊዜዉ የተከሰተ ምጥና ዉርጃ ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡
• የእጅና ፊት ላይ እብጠት፡- የፊትና እጅዎ ላይ እብጠት ከተከሰተ በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የደም ግፊት መጨመር በሽታ ምልክት ሊሆን ይችላል
• ከፍተኛ የሆነ የራስ ምታትና የአይን እይታ ላይ ብዥታ መፈጠር፡- ይህ በእርግዝና ወቅት ለሚከሰት የደም ግፊት መጨመር በሽታ መከሰትና የደም ግፊቱ በጣም ሲጨምር እና ለሚጥል በሽታ አይነት መንቀጥቀጥ(Ecclampsia) ሲያጋልጥ የሚመጣ ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡
• መደበኛ የሆድ ቁርጠት ከ37ኛ ሳምንት በፊት ከተከሰተ፡- ይህ ከቀኑ በፊት የተከሰተ/የመጣ ምጥ ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም ከጨጓራዎ ጋር የተያያዘ ችግር ሊሆን ይችላል፡፡
• ትኩሳት፡- ትኩሳት የኢንፌክሽን መኖር ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡ ኢንፌክሽን በእርግዝናዎ ወቅት መከሰት ፅንሱን ሊጎዳዉ ስለሚችል የህክምና ባለሙያዎን ማማከር ያስፈልጋል፡፡
• የልጁ/የፅንሱ እንቅስቃሴ መቀነስ ካለ፡- ይህ በማህፀን ያለ ልጅዎን መታፈን ወይም በህይወት ያለመኖር አለያም የልጁ በቀስታ መንቀሳቀስ ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡
አንዲት እናት በእርግዝናዋ ወቅት ከላይ ከተጠቀሱት ምልክቶች እንዱ እንኳ በየትኛዉም የእረግዝናዋ ወቅት ካጋጠማት ያለምንም ቅድመሁኔታና ቀጠሮዋን ሳትጠብቅ የህክምና ባለሙያዋን ማማከርና ተገቢዉን ህክምና ማግኘት ይጠበቅባታል፡፡
ምንጭ:- ጤናችን