ቻይናዊው ከ700 በላይ ባለቤት አልባ ውሾችን በመንከባከብ “የውሾች ጠበቃ” ተብለዋል

                                                       

ቻይናዊው ላለፉት 8 ዓመታት ከ700 በላይ ባለቤት አልባ ውሾችን በመንከባከባቸው የውሾች ጠበቃ ተብለዋል።

ዡ ዩሶንግ ይባላሉ፤ በተግባራቸው ምክንያትም የውሾች ጠበቃ የሚል ስሜያ ተሰጥቷቸዋል።

በሄናን ግዛት ዠንግዙ ከተማ የኖሩት እኝህ ግለሰብ ያለፉትን ስምንት ዓመታት የእንስሳት መንክባከቢያ ማዕከል በመክፈት ባለቤት አልባ የጎዳና ውሾችን እየተንከባከቡ ናቸው።

በፈረንጆቹ 2008 በመንገድ ዳር ተጎድቶ ያገኙትን ባለቤት አልባ ውሻ በማንሳት ነው መልካም ተግባራቸውን የጀመሩት።

ውሻው በጉዳና ላይ በሚኖርበት አጋጣሚ በመኪና ተገጭቶ ጉዳት ከደረሰበት በኋላ የስቃይ ጊዜን እያሳለፈ ነበር።

ሁሉም ሰው ትኩረት የነፈገውን ባለቤት አልባ ውሻ ዡ ዩሶንግ እንደ ልጃቸው ከወደቀበት አንስተው፥ በአቅራቢያ ወደሚገኝ የውሾች የህክምና ማዕከል ወስደው አሳከሙት።

ህይወቱን ከታደጉት በኋላ በመኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ የውሾች መጠለያ ሰርተው እንዲኖር አደረጉ።

በጎ ተግባራቸውን አጠናከርውም በርካታ የጎዳና ውሾችን እያነሱ ወደመጠለያው እያመጡ መንከባከብን ቀጠሉበት።

ለውሾች ህክምና እና ምግብም በየወሩ እስከ 200 ዩዋን መመደብ ጀመሩ

በዚህ ብቻ መወሰናቸው ያላስደሰታቸው ቻይናዊው የውሾች ጠበቃ፥ ጓደኞቻቸው 800 ሺህ ዩዋን ወይም 122 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው በማድረግ አዲስ የእንስሳት መንክባከቢያ ማዕከል ከፈቱ።

የማዕከሉን መከፈት ተከትሎ ዡ ስራውን በአግባቡ እየመሩ በርካታ የጎዳና ውሾችን ወደ ማዕከሉ መቀላቀል ጀመሩ።

ላለፉት ስምንት ዓመታትም ከ700 በላይ ባለቤት አልባ የጎዳና ውሾችን በመንክባከብ ላይ ይገኛሉ።

በእነዚያ ዓመታት ምንም ዓይነት እረፍት አልነበራቸውም፤ ቀን እና ሌሊቱን የውሾችን ደህንነት በማረጋገጥ ነው የሚያሳልፉት።

ሰውየው ውሾችን በመመገብ፣ መኖሪያቸውን በማፅዳት ተገቢውን ህክምን እንዲያገኙ በማድረግ፣ ተገናኝተው እርስ በእርስ እንዳይነካከሱ በመነጣጠል እና መጠለያቸውን በማደስ ነው ውሏቸውን የሚያሳልፉት።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement