NEWS: የብራዚሉ ፕሬዚዳንት ሚሼል ቴመር ተጨማሪ የወንጀል ክስ ቀረበባቸው

                                             

የብራዚል ከፍተኛ የፀረ ሙስና አቃቤ ህግ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሚሼል ቴመርን ህግን በመጣስ እና በሙስና ወንጀል አንደከሰሳቸው ተነግሯል።

ፕሬዚዳንቱ የወንጀል ክስ ሲቀርብባቸው ይህ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑም ተነግሯል።

አቃቤ ህግ፥ ፕሬዚዳንት ቴመርን ጉቦ በመቀበል እና ምስክሮች ምንም ነገር እንዳይናገሩ በገንዘብ ለመግዛት ሞክረዋል የሚል የሙስና ወንጀሎች ነው የከሰሳቸው።

የብራዚሉ ፕሬዚዳንት ሚሼል ቴመር ቀረበባቸውን ውንጀላ ውድቅ ያደረጉ ሲሆን፥ አግባብነት የሌለው እና ትክከል ያልሆነ ስራ ነው ሲሉም አጣጥለዋል።

ከዚህ ቀደም በፕሬዚዳንቱ ላይ ቀርቦ የነበረው የሙስና ክስ በሀገሪቱ ኮንግረስ ውድቅ መደረጉ የሚታወስ ሲሆን፥ ኮንግረሱ ፕሬዚዳንቱ ፍርድ ቤት ይቅረቡ አይቅረቡ የሚለው ላይ የመወሰን ስልጣን አለው።

ፕሬዚዳንት ሚሼል ቴመር ለሁለተኛ ጊዜ በቀረበባቸው ክስ ላይ ብቻቸውን አይደለም የተከሰሱት የተባለ ሲሆን፥ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ስድስት ተጨማሪ ፖለቲከኞች ተከሰዋል።

ጠቅላይ አቃቤ ሀግ ሮድሪጎ ጃኖት፥ ፕሬዚዳንት ቴመር የሚያደርጉት ተግባር አንድ የወንጅልኛ ድርጀት መሪ ከሚያደርገው ጋር ተመሳሳይ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በፕሬዚዳንቱ የሚመራው ቡድንም ከተለያዩ ኩባንያዎች የ190 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ጉቦ ተቀብለዋል ሲሉም ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ገልፀዋል።

በዚህ ዙሪያም ጉቦ ለመስጠት የተገደዱ ሰዎች ቃላቸውን መስጠታቸውን ነው ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ያስታወቁት።

የፕሬዚዳንት ቴመር ጠበቆች በበኩላቸው፥ በፕሬዚዳንቱ ላይ የቀረቡት ክሶች ተአማኒ አይደሉም ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ በፕሬዚዳንቱ ላይ የቀረበው ክስ ለሀገሪቱ የታችኛው ምክር ቤት ተልኮ ክርክር ሳይደረግበት በፊት መጀመሪያ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ቀርቦ ተቀባይነት ማግኘት ይጠበቅበታል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement