NEWS: ፓሪስና ሎስ አንጀለስ የ2024ና የ2028 ኦሎምፒክን እንዲያስተናግዱ ተመረጡ

                                                        

የፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስና የአሜሪካዋ ሎስ አንጀለስ የ2024 እና የ2028 የኦሎምፒክ ውድድሮችን እንዲያስተናግዱ መመረጣቸውን ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ አስታወቀ።

ሁለቱ ከተሞች ከዚህ በፊት የ2024 የኦሎምፒክ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ ፍላጎታቸውን ቢያቀርቡም ሎስ አንጀለስ አራት ዓመት ዘግይታ የ2028ቱን አሎምፒክ ለማስተናገድ ተመርጣለች።

ፓሪስ ከዚህ በፊት በ2008 እና በ2012 የኦሎምፒክ ውድድሮችን ለማስተናገድ ፍላጎት ብታሳይም ሳይሳካላት ቀርቷል።

ከተማዋ የ2024ቱን ኦሎምፒክ እንድታስተናግድ መመረጧ በፈረንጆቹ 1924 የአሎምፒክ ጨዋታዎችን ያስተናገደችበትን 100ኛ ዓመት በዓል ድርብ አድርጎላታል።

ሎስ አንጀለስ በአንፃሩ የ1932 እና የ1984 ሎምፒኮችን ማስተናገዷ ይታወሳል።

ዓለም አቀፉ የአሎምፒክ ኮሚቴ የ2024 የኦሎምፒክ ውድድሮችን ማስተናገድ የሚፈልጉ ከተሞችን አወዳድሮ ሃምቡርግ፣ ሮም እና ቡዳፔስት ከውድድር ሲወጡ ፓሪስና ሎስ አንጀለስ ብቻ ነበር የቀሩት።

ኮሚቴው ባሳለፍነው ሰኔ ወር የ2024 አሎምፒክ የምታስተናግደውን ከተማ ለመምረጥ በፔሩ ዋና ከተማ ሊማ ባሳለፈው ውሳኔ፥ የ2028 አሎምፒክን የምታስተናግድን ከተማ ለመመረጥም እቅዱን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ሁለቱ ከተሞች በተከታታይ የኦሎምፒክ ውድድሮችን እንዲያስተናግዱ በሙሉ ድምፅ መመረጣቸውን የዓለም አቀፉ አሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ቶማስ ባች አረጋግጠዋል።

ፓሪስ ከኦሎምፒክ ጨዋታዎች መካከል የአትሌትክስ ስፖርቶችን የ1998 የዓለም ዋንጫና የ2016 የአውሮፓ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታዎችን ባስተናገደው ስታድ ዴ ፍራንስ ለማስተናገድ ነው የወሰነችው።

ሎስ አንጀለስ በበኩሏ የ1932 እና የ1984 የኦሎምፒክ የአትሌቲክስ ውድድሮችን ባስተናገደችበት የሎሰ አንጀለሰ ሚሞሪያል ኮሊሲየም የ2028 ተመሳሳይ መርሃ ግብሮችን ለማካሄድ መርጣለች።

ከተሞቹ ለሌሎች ውድድሮች የሚሆኑ ቦታዎችን በማዘጋጀት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል።

 

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

Advertisement