NEWS: ኢትዮጵያ በ2010 እቅዷ ለኢኮኖሚ ዲፕሎማሲና ለዳያስፖራ ተሳትፎ ልዩ ትኩረት ሰጥታለች

                                      

ኢትዮጵያ በ2010 ዓ.ም በሁለትዮሽ እና ባለብዙ ወገን መድረኮች የምታካሂደውን የውጭ ግኑኝነት እንቅስቃሴ አጠናክራ እንደምትቀጥል ተገለጸ፡፡

የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲና የዳያስፖራ ተሳትፎ ማሳደግም በበጀት ዓመቱ በልዩ ትኩረት ይሰራባቸዋል ተብሏል።

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በሚኒስቴሩ በኩል ስለታቀዱ ዋና ዋና ተግባራት ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

አቶ መለስ እንዳሉት፥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ሚሲዮኖችን፣ የተለያዩ የዘርፍ መስርያ ቤቶችንና አጋር ተቋማትን በማስተባብር በበጀት አመቱ የአገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም የሚያስከብር የዲፕሎማሲ ድል ለማስመዝገብ በቅንጅት ይሰራል።

ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ጥቅሟና መብቷ እንዲጠበቅ፣ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ያላት መልካም ቅርበት እንዲጠናከር፣ የዳያስፖራው ተሳትፎና መብት እንዲረጋገጥ፣ በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ በኩል ኢንቨስትመንት በመሳብ፣ ገበያና የፋይናንስ ድጋፍ በማፈላለግ፣ ቱሪስቶችን በመሳብ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር በማድረግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተግቶ ይሰራልም ብለዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን በማስፈን፣ ውክልናን በማስፋት እና አጋርነቶችን በመመስረት በኩል ብዙ እንደተሰራ ተገልጿል።

እንዲሁም በዓለም አቀፍ መድረኮች ተደማጭነት በማሳደግና የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችል ተግባር በዲፕሎማሲው ረገድ መከናወኑን በመጠቆም በያዝነው ዓመትም ትኩረት የሚሰጣቸው ተግባራት መሆናቸውን ተጠቁሟል።

“ኢትዮጵያ ለብቻዋ በአፍሪካ ቀንድ የሰላም እና የብልፅግና ደሴት መሆን አትችልም” ያሉት ቃል አቀባዩ፥ ከጎረቤቶቻችን ጋር በሚደረግ ሁለንተናዊ ግንኙነት በአገራችን እየተካሄደ ላለው ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ገልጿል።

 

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

Advertisement