NEWS: በቆሼ ቁሳቁስ ሲለቅሙ ከነበሩ ሰዎች አንዱ የቆሻሻ ክምር ተደርምሶ ህይወቱ አለፈ

                                       

በበላይ ተስፋዬ

በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው የቆሻሻ ማከማቻ ስፍራ ቁሳቁስ በመልቀም ላይ ከነበሩ ሰዎች አንዱ በቆሻሻው መደርመስ ህይወቱ አልፏል።

ዛሬ ከቀኑ 6 ሰዓት ከ15 ደቂቃ አካባቢ ሁለት ግለሰቦች በቦታው በተቆለለ የቆሻሻ ክምር ስር ቁሳቁስ በመልቀም ላይ እያሉ ነው ክምሩ የተደረመሰው።

በስፍራው ከነበሩት ሁለት ግልሰቦች አንዱ ሩጦ ህይወቱን ሲያተርፍ፥ ሁለተኛው ግለሰብ ግን ቆሻሻው ተደርምሶበታል።

የእሳትና ደንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት፥ ቆሻሻ የተደረመሰበትን ግለሰብ ህይወት ለማትረፍ ጥረት ተደርጎ ነበር።

በአካባቢው የሚገኙ የባለስልጣኑ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ባለሙያዎች፥ የተለያዩ ማሺነሪዎች እና አምቡላንስ በመያዝ ወደ ቦታው ላይ ተገኝተው ቆሻሻውን ከግለሰቡ አንስተው ህይወቱን ለማትረፍ ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

ሟች ዕድሜው ከ35 እስከ 40 የሚገመት ሲሆን፥ የተለያዩ ቁሳቁሶችን በመለቃቀም የሚተዳደር መሆኑ ታውቋል።

አስክሬኑ ለተጨማሪ ምርመራ ለፖሊስ ተስጥቷል ነው የተባለው።

የሚመለከተው አካል መሰል አደጋዎች እንዳይከሰቱ አካባቢውን በጊዜያዊነት በማጠር ቆሻሻውን በዘላቂነት ማንሳት እንዳለበት አቶ ንጋቱ ማሞ ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ በህይወቱ ላይ አደጋ ከሚያስከትሉ አካባቢዎች ራሱን በማራቅ ደህንነቱን መጠበቅ ይገባል ነው ያሉት።

ከዚህ ቀደም መጋቢት 2 ቀን 2009 ዓ.ም አመሻሽ ላይ በቆሼ በደረሰ የቆሻሻ መደርመስ አደጋ ከ110 የሚበልጡ ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

 

 

 

 

Advertisement