NEWS: በመዲናዋ የተጀመሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ግንባታ ለማጠናቀቅና አዳዲስ ግንባታዎችን ለማስጀመር የ20 ቢሊየን ብር ብደር ተፈቀደ

                                         

በበላይ ተስፋዬ

በአዲስ አበባ የተጀመሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ግንባታ ለማጠናቀቅና አዳዲስ ግንባታዎችን ለማስጀመር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ20 ቢሊዮን ብር ብድር ተፈቀደ።

የተፈቀደው ገንዘብ 132 ሺህ የ40/60 እና የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ግንባታ በማጠናቀቅ ከተያዘው ዓመት ጀምሮ ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ የሚያስችል መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ አስታውቋል።

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር ዶክተር አንባቸው መኮንን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በቂ ብድር ከንግድ ባንክ በመገኝቱ የቤቶቹ ግንባታ የገንዘብ እጥረት አያጋጥማቸውም ብለዋል።

የተጀምሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በማጠናቀቅ ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ የሚያስችልና አዳዲስ ግንባታዎች ለመጀመር የሚያስችል 20 ቢሊየን ብር መፈቀዱንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

መንግስት የገንዘብ ብድሩን ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ሲያቀርብ የቤቶቹ ግንባታ በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለተጠቃሚዎች እንዲተላለፉ ለማድረግ መሆኑንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

ብድሩ የተፈቀደው በፋይናንስ አቅርቦት እጥረት ግንባታዎች ተጓተቱ የሚለውን ምክንያት ለማስቀረት መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

በመሆኑም ሌሎች የግንባታ ሂደቱን የሚያጓትቱ አሰራሮች ተቀባይነት አይኖራቸውም ያሉት ሚኒስትሩ፥ የቤቶቹ የግንባታ ሂደትም ጥብቅ ክትትል የሚደረገብት ይሆናል ብለዋል።

በመዲናዋ ያለውን የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍም አዳዲስ አማራጮችን የማጥናትና ተግባራዊ የማድረግ አርምጃ በመንግስት እንደሚወሰድም ዶክተር አንባቸው መኮንን አስታውቀዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ 140 ሺህ ሰዎች የ40/60 እና ከ700 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ በ20/80 በጋራ መኖሪያ ቤት መርሃ ግብር ተመዝግበው በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።

አብዛኛዎቹ ባለሶስት መኝታና ስቲዲዮ ቤቶች ለባለዕድለኞች የተላለፉ በመሆኑ አሁን በግንባታ ላይ ያሉ 132 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የ40/60 እና 20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ናቸው።

የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ አቶ ይድነቃቸው ዋለልኝ፥ አሁን የተፈቀደው የ20 ቢሊየን ብር ብድር 132 ሺ ቤቶች ግንባታ አጠናቆ ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ ያስችላል ብለዋል።

ከ1997 ዓ.ም ወዲህ በሀለቱ መርሃ ግብሮች ተመዝግበው የጋራ መኖሪያ ቤት የሚጠባበቁ 80 ሺህ ነባር ተመዝጋቢዎች ደግሞ ከእነዚህ ቤቶች በቅድሚያ የሚያገኙ መሆናቸውንም ገልፀዋል።

በብድር የተገኘው ገንዘብ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለ2010 በጀት ዓመት ከመደበው በጀት 50 ከመቶ እንደሚሆንም ነው አቶ ይድነቃቸው የተናገሩት።

በአዲስ አበባ የመኖሪያ ቤት አቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጠምን ለመቅረፍና የስራ ዕድል ለመፍጠር ነበር ከ12 ዓመት በፊት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ የተጀመረው።

የቤት መርሃ ግብሩ ከጀመረ ወዲህ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ከ175 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በአዲስ አበባ ከተማ ተገንብተው ለተጠቃሚዎች ተላልፈዋል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

Advertisement