NEWS: የኦሮሚያ ክልል በ2010 በጀት ዓመት ለ1 ሚሊየን ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ማቀዱን አስታወቀ

                                       

የኦሮሚያ ክልል በ2010 በጀት ዓመት ለ1 ሚሊየን ስራአጥ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ማቀዱን ክልሉ የስራ እድል ፈጠራና የከተሞች የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አስታወቋል፡፡

የኤጀንሲው ምክትል ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ገለታ፥ በበጀት ዓመቱ ለ750 ሺህ ወጣቶች ቋሚ እና ለ250 ሺህ ጊዜያዊ የስራ እድል ለመፍጠር እቅድ ተይዞ፥ እስከታች ባለው መዋቅር አማካይነት ወጣቶችን የመለየት ስራ ተጀምሯል ብለዋል ፡፡

ኤጀንሲው በገጠር እና በከተማ ያለውን የስራ እድል ቅድመ ጥናት ማድረጉን የተናገሩት አቶ ጌታቸው፥ በዚሁ መሰረት ወጣቶቹ በግብርና፣ በግንባታ፣ በማምረቻ፣ በአገልግሎት እና ንግድ ስራ ላይ እንደሚሰማሩ ነው የገለፁት።

በተለይ በማምረቻው ዘርፍ የሚሰማሩና ከዩኒቨርሲቲ፣ ከቴከኒክ ሙያ ትምሀርት እና ስልጠና ኮሌጅ በ2009 ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ 43 ሺህ ወጣቶችን የመለየት ስራ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

ወጣቶቹ የተሟላ የድጋፍ ማዕቀፍ እንዲያገኙ በገጠር ለማምረቻ እና መሸጫ የሚሆን፥ 61 ሺህ ሄከታር መሬት በከተማ 1 ሺህ 200 ሄክታር መሬት እና 5 ሺህ ሼዶች በመስራት ለወጣቶቹ ለማስተላለፍ እቅድ ተይዟል፡፡

ከዚሀም በተጨማሪ ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በተባበር የ5 ነጥብ 1 ቢሊየን ብድር ለመስጠት ተቅዷል ነው የተባለው።

በክልሉ በተጠናቀቀው የ2009 በጀት ዓመት ለ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ወጣቶች የስራ እድል መፈጠሩም ይታወቃል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement