NEWS: አሜሪካ የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ሃብትና ንብረት እንዲታገድ ትፈልጋለች

                                           

አሜሪካ በሰሜን ኮሪያ ላይ ያነጣጠረ ጠንካራ ማዕቀብን የተባበሩት መንግስታት ድርጀት የፀጥታው ምክር ቤት እንድዲያፀድቅ እየጎተጎተች ነው።

ፒዮንግያንግ ስድስተኛውን የኒዩክሌር ቦምብ ሙከራ በተሳካ ሁኔታ ማካሄዷን ተከትሎ የማዕቀቡ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳቡም በዋሽንግተን አቅራቢነት ለሁሉም የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ተዳርሷል።

ሰሜን ኮሪያ ከኒዩክሌር ቦምብ ሙከራዋ ባሻገር ተደጋጋሚ የሚሳኤል ማስወንጨፍ ድርጊቷን ኣላቆመችም።

በኪም ጆንግ ኡን የምትመራው ሀገር ድርጊት ያሰጋቸው አሜሪካና ደቡብ ኮሪያም ስርዓት የሚያስይዘ ከበድ ያለ ማዕቀብ እንዲጣልባት እየጎተጎቱ ነው።

ቻይናና ሩሲያ በበኩላቸው ማዕቀቡን እንደሚቃወሙ የሚጠበቅ ሲሆን፥ የዲፕሎማሲ መንገድ ብቸኛው አማራጭ ነው የሚል አቋማ አላቸው።

በእነዚህ ሁለት አቋሞች መካከል ግን ፒዮንግያንግ አሁንም የሃይድሮጅን ቦምብ ማምረቷንና አሜሪካን የሚጎዳ ጥቃት ለመሰንዘር ዝግጁ መሆኗን መግለጿን ቀጥላለች።

በአሁኑ ወቅት የሚሳኤልና የሃይድሮጅን ቦምብ ሙከራዋን እንድታቆምና የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ የማምረት መርሃ ግብሯን እንድታቋርጥ በሚል በመንግስታቱ ድርጅት የተለያዩ ማዕቀቦች ተጥለውባታል።

ባሳለፍነው ነሃሴ ውር የድንጋይ ከሰል እና ሌሎች ምርቶችን ወደ ውጭ ገበያ እንዳትልክ የሚከለክል ማዕቀብ በመጣሉ፥ ሀገሪቱ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶች ልታገኝ የምትችለውን አንድ ቢሊየን ዶላር ገቢ አጥታለች።

ይህም ከአጠቃላይ የወጪ ንግድ ገበያዋ አንድ ሶስተኛውን ድርሻ ይይዛል።

ሆኖም የተወሰኑ የንግድ ቀጠናዎቿ ነፃ በመሆናቸው ሙሉ በሙሉ የምትፈልገውን አጥታለች ለማለት አያስደፍርም።

ሰሞኑን አሜሪካ ያዘጋጀችው አዲስ የማዕቀብ የውሳኔ ሃሳብም ሰሜን ኮሪያ፥ ከማንኛውም ሃገር የነዳጅ ምርት እንዳታገኝ ማድረግንና ወደ ውጭ የምትልከውን የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ምርቶች ሙሉ በሙሉ ማገድን ያካተተ ነው።

የመሪዋን የኪም ጆንግ ኡንን እና የሚመሩትን መንግስት ሃብትና ንብረት እንዳይንቀሳቀስ ማገድም በረቂቅ የውሳኔ ሀሳቡ ተካቷል።

ከዚህም ባሻገር ኪም ጆንግ ኡን እና ሌሎች የሰሜን ኮሪያ ባለስልጣናት ምንም ዓይነት ጉዞ እንዳያደርጉ መከልከልም አሜሪካ ያቀረበችው የማዕቀብ ረቂቅ አካል ነው።

በረቂቁ ላይ ሰሜን ኮሪያውያን ሰራተኞች በማንኛውም ሌላ ሀገር ሄድው እንዳይሰሩ ክልከላ መጣሉም የጉዳት አድማሱ ሰፊ መሆኑን ማሳያ ነው ተብሏል።

በአሁኑ ወቅት ፒዮንግያንግ በውጭ ከሚኖሩ ዜጎቿ ከሚላክ ገንዘብና ወደ ውጭ ከምትልካቸው የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች የምታገኘው ገቢ ነው ኢኮኖሚዋን እየደጎመ የሚገኘው።

አሜሪካ በሰሜን ኮሪያ ላይ የጉዳት አድማሱ ሰፊ የሆነውን የማዕቀብ ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብ ብታቀርብም፥ ከሩሲያና ከቻይና በኩል ተቃውሞ ሊገጥማት እንደሚችል ይጠበቃል።

ቤጂንግና ሞስኮ በአሁኑ ውቅት ለሰሜን ኮሪያ የነዳጅ ምርት እያቀረቡ የሚገኙ ሲሆን፥ በፀጥታው ምክር ቤትም ድምፅን በድምፅ የመሻር ስልጣን አላቸው።

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሀገራቸው አሁን ለሰሜን ኮሪያ እያቀረበች ያለው 40 ሺህ ቶን የነዳጅ ምርት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም የሚል አቋም አላቸው።

ከዚህ አንፃር የነዳጅ አቅርቦት ማእቀቡ ፋይዳ ቢስ መሆኑን ነው ፑቲን ያነሱት።

ቻይና በበኩሏ የሰሜን ኮሪያና የአሜሪካ ዋነኛ የንግድ አጋር ስትሆን በፒዮንግያንግ ላይ ከዚህ ቀደም በተጣሉ ማዕቀቦች ላይ የተወሰነ ድጋፍ ማሳየቷ አይዘነጋም።

ሆኖም ቤጂንግ እንደ ሞስኮ ሁሉ ከማዕቀብ ይልቅ ሌሎች የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ማተኮር እንደሚገባ አቋሟን አንፀባርቃለች።

ሩሲያና ቻይና በአሜሪካና በወዳጇ ደቡብ ኮሪያ የሚደረጉ ወታደራዊ ልምምዶች እንዲቆሙ የጠየቁ ሲሆን፥ በሴኡል እየተከናወነ የሚገኘው የሚሳኤል መቃወሚያ ተከላ ስራም እንዲሰረዝ ይፈልጋሉ።

ሰሜን ኮሪያ ከኒዩክሌር ጦር መሳሪያ መርሃ ግብሯ እንድታቆም ከተፈለገ አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ ከፀብ አጫሪ አድርጎታቸው ሊታቀቡ ይገባል ነው የሚሉት።

ዋሽንግተንና ሴኡል በበኩላቸው የሞስኮንና የቤጂንግን የመፍትሄ ሀሳብ ውድቅ አድርገውታል።

አሜሪካ ለፀጥታው ምክር ቤት ያቀረበችው የማዕቀብ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ በምክር ቤቱ ካልፀጸደቀ የራሷን ማዕቀብ ለመጣል አቅዳለች።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ቀደም ሀገራቸው ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ሊያቋርጡ እንደምትችል መናገራቸው አይዘነጋም።

የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር የንግድ ግንኙነቱን በመሰረዝ ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመፍጠር የሚያስችለው እቅድ፥ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ወደ ፕሬዚዳንቱ ሊመራ ዝግጁ መሆኑን ጠቁሟል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

Advertisement