NEWS: የኦሮሚያ ገቢዎች ባለስልጣን ከ10 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰቡን አስታወቀ

                                               

የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ10 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰቡን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ በ2009 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም ግምገማና በአዲሱ የበጀት ዓመት እቅድ ላይ ለመምከር ያዘጋጀው የ5 ቀን የውይይት መድረክ ከበአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አህመድ ቱሳ በወቅቱ እንደገለፁት፥ ባለስልጣኑ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ10 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ በመሰብቡን ተናግረዋል።
የተሰበሰበው ከዓመታዊ ዕቅዱ 88 ነጥብ 3 በመቶ ማሳከቱን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

“በክልሉ የነበረው ወቅታዊ የፀጥታ ችግር፣ የግብር ከፋዩ ግንዛቤ በሚፈለገው ደረጃ ያለመለወጥና ተያያዥ ማነቆዎች ለእቅዱ ሙሉ በሙሉ ያለመሳካት ምክንያት ናቸው” ብለዋል። 

በተያያዘ በኦሮሚያ ክልል በዕለት የገቢ ግምት በተጣለባቸው ግብር ቅሬታ ላቀረቡት ከ86 ሺህ በላይ የደረጃ ሐ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች ምላሽ መሰጠቱንም አቶ አህመድ ገልጸዋል።

ከእለት ገቢ ግምት የግበር ትመና ጋር ተያይዞ ቅሬታ ካቀረቡት 94 ሺህ 508 ግብር ከፋዮች መካከል ከ86ሺህ በላይ ለሚሆኑት ምላሽ መሰጠቱንም አስታውቀዋል።

ምላሽ ከተሰጣቸው መካከል ከ46 ሺህ በላይ የሚሆኑት ጉዳያቸው ተጣርቶ ማስተካከያ ተደርጎላቸዋል ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ።

እንዲሁም 42 ሺህ 552 የሚሆኑት ቀደም ሲል የተጣለባቸው የግብር መጠን እንዲፀና መደረጉን ተናግረዋል።

“በክልሉ ከ2003 በጀት አመት ጀምሮ ምንም አይነት የዕለት ገቢ ሽያጭ ተመን አልተደረገም “ያሉት አቶ አህመድ በዘንድሮ ዓመት የዕለት ሽያጭ የገቢ ተመንን ተግባራዊ በማድረግ ከ319 ሺህ በላይ ግብር ከፋዮች በዚሁ አሰራር እንዲያልፉ መደረጉን ተናግረዋል።

እንደ አቶ አህመድ ገለፃ ከግብር ከፋዮች መካከል ቅሬታ ያቀረቡት 29 በመቶ ሲሆኑ 71 በመቶዎቹ ቀድሞ በዕለት ገቢ ግምት የተጣለባቸውን ግብር በወቅቱ ከፍለዋል።

በእስካሁኑ ሂደት የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች ከ80 በመቶ በላዮቹ ግብራቸውን መክፈላቸውን ያስረዱት ሃላፊው፥ ከነዚሁ ግብር ከፋዮች 1 ቢሊyን የሚጠጋ የግብር ገቢ ተሰብስቧል” ብለዋል ።

በአዲሱ የበጀት ዓመት ከማዘጋጃ ቤት፣ ከቀረጥና ታክስ ከ13 ቢሊyን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን አመላክተዋል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement