NEWS: የብራዚል የቀድሞ ሁለት ፕሬዚዳንቶች ላይ ክስ ተመሰረተ

                                              

የብራዚል የቀድሞ ሁለት ፕሬዚዳንቶች በሙስና ወንጀል በይፋ ክስ ተመሰረተባቸው።

የሃገሪቱ ከፍተኛ አቃቢ ህግ ሮድሪጎ ጃኖት፥ በቀድሞዎቹ የሃገሪቱ ፕሬዚዳንቶች ዲልማ ሩሴፍ እና ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ ላይ በይፋ የሙስና ክስ መስርተዋል።

ከመሪዎቹ በተጨማሪም ስድስት የብራዚል የሰራተኞች ፓርቲ አባላት ላይም ክሱ ተመስርቷል ነው የተባለው።

መሪዎቹ ከሃገሪቱ ግዙፍ ነዳጅ አቅራቢ ኩባንያ ፔትሮብራስ ገንዘቦችን በህገ ወጥ መልኩ ለግል ጥቅም ማዋል የሚያስችል ህጋዊ ያልሆነ ተቋም በማቋቋም፣ ጉቦ በመቀበልና በህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀል ነው ክስ የተመሰረተባቸው።

ከሚካሄዱ ግንባታዎች ጋር ተያይዞም ለፔትሮብራስ ስምምነቶችን ተገቢ ባልሆነ መንገድ አሳልፎ በመስጠት በከፍተኛ ክፍያ እንዲከናወን ማድረጋቸውም ተጠቅሷል።

ከፈረንጆቹ 2002 እስከ 2016 ድረስ ተፈጽሟል በተባለው ወንጀልም፥ የሰራተኞች ፓርቲ በህገ ወጥ መንገድ 475 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በህገ ወጥ መልኩ መመዝበሩ ተገልጿል።

በበርካቶች ዘንድ ጠንካራ ፖለቲከኛ ተደርገው የሚታዩት ሉላ ዳ ሲልቫ ግን የቀረበውን ውንጅላ አስተባብለዋል።

የእርሳቸው ጠበቃም የዳ ሲልቫን ስም ለማጉደፍና የቀጣዩን ምርጫ እቅዳቸውን ለማክሸፍ ህጉ አላግባብ ተተርጉማል ሲል ቅሬታውን ገልጿል።

ሉላ ዳ ሲልቫ ባለፈው ሃምሌ ወር በቀረበባቸው የሙስና ወንጀል የ9 አመት ከ6 ወራት የእስር ቅጣት ተፈርዶባቸው ነበር።

በወቅቱ ሉላ ፔትሮብራስ ጨረታ እንዲያሸንፍ በማድረግ፥ ለውለታቸው የመኖሪያ አፓርታማ በጉቦ መልክ ተቀብለዋል በሚል ነበር የተከሰሱት፡፡

እርሳቸው ኦ ኤ ኤስ የተባለው የሃገሪቱ ምህንድስና ኩባንያ ከፔትሮብራስ ጋር ውል እንዲፈፅም ለማድረግ የአፓርታማውን ጉቦ በመቀበላቸው ነበር የተወነጀሉት።

የሰራተኞች ፓርቲም ክሱ መሰረተ ቢስና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ጉዳዩን ይዞም ወደ ሃገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደሚያመራም ፓርቲው ጠቅሷል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement