NEWS: የጌጣ ጌጥ ማዕድናት ወደ ውጭ ሀገር በመሸጥ የተሰማሩ ባለሀብቶች የውጭ ዜጎች በፈጠሩብን ችግር ከገበያው ለመውጣት እየተገደድን ነው ሲሉ ለሸገር ተናገሩ፡፡

                                     

ዮሐንስ የኋላወርቅ

ስማችንና ድምፃችን ይቅር ችግራችንን ግን ንገሩልን ብለው የነገሩን ነጋዴዎች እንዳሉት ከሆነ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ወደ ውጭ ለመሄድ እንደሚፈፅሙት ያለ የውሸት ጋብቻ ከጌጣጌጥ ማዕድን አውጪዎች ጋር በመፈፀም ለኢትዮጵያውያኑ ብቻ በተፈቀደው የጌጣጌጥ ማዕድናት ማውጣት ዘርፍ ላይ እየተሰማሩ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የማዕድን ማውጣት ፈቃድ በመከራየትና ማዕድናቱ በሚወጡባቸው አካባቢዎች ለስድስት ወርና ለአንድ አመት ያህል ቤት በመከራየት ጭምር ማዕድኑን በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ሀገራቸው እየላኩ መሆኑንም ነግረውናል፡፡

የሕንድና የፓኪስታን ዜጎች ናቸው የተባሉት እነዚህ ሕጋዊ ያልሆኑ የውጭ ዜጎች ከማዕድን አውጪዎቹ በከፍተኛ ገንዘብ ማዕድኑን እየገዙ እኛን ከገበያው እያስወጡ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በቱሪዝም ሰበብም የሚገቡ የውጭ ዜጎች ቀጥታ ገበሬው ጋር በመሄድ የጌጣ ጌጥ ማዕድንን እንደሚገዙ ነግረውናል፡፡

ይህ ሁሉ የሚሆነው የፌዴራሉና የክልል ማዕድን ቢሮዎች ተገቢውን ክትትልና ቁጥር ባለማድረጋቸው እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

አስተያየት ሰጪዎቹ በተለይም ነገሩ ዝም ከተባለ ነገ ጉዳዩ ወደ ተደራጀ ውንብድና እና ወንጀል ሊያድግ ሁሉ ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ነግረውናል፡፡

ስለ ጉዳዩ የጠየቅናቸው የማዕድን ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሣ በእርግጥም ችግሩ መኖሩን አምነው እነዚህ የተባሉት የውጭ ዜጎች እንዳይገቡ ለጊዜው አግደናቸዋል ብለዋል፡፡

በውሸት ጋብቻ ላይ የተሳሰሩት ላይም አጣርተን እርምጃ እንወስዳለን ሲሉም ነግረውናል፡፡
ይሁን እንጂ ዘላቂ መፍትሄ ይሆን ዘንድ የውጭ ዜጎቹ እንዴት ባለ መልኩ ወደ ሃገር ቤት መግባት ይችላሉ? እንዴትስ የጌጣ ጌጥ ማዕድኑ ሊሸጥላቸው ይችላል? ለሚለው መመሪያ እየተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በተለይም ሳፋየርና ኢምራልድ የተባሉት የጌጣጌጥ ማዕድናት እጅግ ተፈላጊ መሆናቸውንም ሰምተናል፡፡

ምንጭ:- የሸገር FM 102.1 ሬዲዮ

Advertisement