NEWS: ከ51 ሚሊየን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ የኢታኖል ማምረቻ ፋብሪካ ሊገነባ ነው

                                  

ከ51 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጪ የሚደረግበት የኢታኖል ማምረቻ ፋብሪካ በወንጂ ሊገነባ ነው።

ከወንጂ ስኳር ፋብሪካ የሚወጣውን የሞላሰስ ምርት ወደ ኢታኖል ቀይሮ ለማምረት የሚያስችለው ፋብሪካ ከጀርመኑ ኡገን ሸሚት ኩባንያ ጋር በትብብር ነው የሚገነባው።

የፋብሪካው 83 በመቶ ድርሻ የጀርመኑ ኩባንያ ሲሆን፥14 በመቶው የመንግስት ቀሪው ሶስት በመቶ ደግሞ በሌሎች ሶስት ባለድርሻዎች የተያዘ ነው።

ፋብሪካውን ለመገንባት 51 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ የሚያስፈልግ ሲሆን፥ ግንባታው በሁለት ዙር የሚካሄድ ይሆናል።

የመጀመሪያው ዙር በአዲሱ አመት መጀመሪያ ተጀምሮ በዚያው አመት የሚጠናቀቅ ሲሆን፥ ሁለተኛው ዙር ግንባታ ደግሞ በ2011 ዓ.ም እንደሚጀመር፥ በስኳር ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ አቶ ጋሻው አይችሉህም ተናግረዋል።

አሁን ላይም የፋብሪካውን ግንባታ ለመጀመር ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል፤ የፋብሪካው የመጀመሪያ የግንባታ ምዕራፍ ሲጠናቀቅ በቀን 30 ሺህ ሊትር ኢታኖል የማምረት አቅም እንደሚኖረውም ይጠቅሳሉ።

ሁለተኛው ግንባታ ሰጠናቀቅ ደግሞ ሀገሪቱ በቀን 60 ሺህ ሊትር ኢታኖልን የሚያመርት ፋብሪካ ባለቤት ትሆናለች ነው ያሉት።

አሁን ላይ ኢትዮጵያ ከፊንጫ እና መተሃራ ስኳር ፋብሪካ ከሚገኝ ሞላሰስ ብቻ ኢታኖልን ታገኛለች።

ፋብሪካው ሃገሪቱ የኢታኖል ነዳጅ ድብልቅን በመጠቀም በውጭ ምንዛሪ የምታስገባውን የነዳጅ መጠን ለመቀነስ እንደሚረዳትም ይታመናል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

Advertisement