NEWS: የ2009 በጀት አመት የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት የወጪ ንግድ አፈጻጸም ከእቅድ በታች ነው

                                           

የ2009 በጀት አመት የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት የወጪ ንግድ አፈጻጸም ከተያዘው እቅድ በታች ሆኗል።

በ2009 በጀት አመት በጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት አፈፃፀም ዙሪያ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።

በምክክር መድረኩ ላይ ኢትዮጵያ በበጀት አመቱ ከጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምርቶች 271 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት አቅዳ እየሰራች መሆኑ ተጠቅሷል።

ይሁን እንጅ በበጀት አመቱ ወደ ውጪ ከተላኩ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምርቶች 89 ነጥብ 3 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር መገኘቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በሪፖርቱ አስታውቋል።

ይህ አፈጻጸምም የእቅዱን 32 ነጥብ 9 በመቶ ብቻ ይሸፍናል።

ከተገኘው ገቢ ውስጥም 25 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላሩ በሃገር ውስጥ ባለሃብቶች የተገኘ ሲሆን፥ ይህም የእቅዱን 29 በመቶ ድርሻ ይይዛል ነው ያለው።

የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራቾች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ፋሲካ ታደሰ በበኩላቸው፥ በበጀት አመቱ 64 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር መገኘቱን ይጠቅሳሉ።

ይህም አምና ከተገኘው 78 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ጋር ሲነጻጸር ያነሰ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በበኩሉ በማህበሩ የቀረበውን ሪፖርት እንደማይቀበለው ገልጿል።

ከስራ እድል ፈጠራ አኳያም ለ34 ሺህ ዜጎች በዘርፉ የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ17 ሺህ 447 ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል ነው ያለው።

ባለሃብቶች ምርታቸውን ለሃገር ውስጥ ገበያ ማቅረባቸው፣ በዘመናዊ የአመራረት ዘይቤ ላይ የሚስተዋሉ የቴክኒክ ችግሮች፣ ለዘርፉ የሚደረገው ማበረታቻ ዝቅተኛ መሆን፣

ጥራቱን ያልጠበቀ ጥጥ አቅርቦት እና ችግሮች ሲከሰቱ ፈጥኖ መፍትሄ አለመስጠት ለገቢው መቀነስ ምክንያት ነው ተብሏል።

ይህ ሁኔታም ባለሃብቶችን በውጪ ገበያ ተወዳዳሪ እንዳላደረጋቸውም ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው።

የኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራቾች ማህበር፥ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ምርቶችን ለውጪ ገበያ ከመላክ ይልቅ ከተለያዩ ሃገራት እንደምታስገባ ይገልጻል።

በዚህም ባለፈው አመት ብቻ 800 ሚሊየን ዶላር ዋጋ ያላቸው የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምርቶች ወደ ሃገር ውስጥ ገብተዋል ነው ያለው፤ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ200 ሚሊየን ዶላር ብልጫ እንዳለው በመጥቀስ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ቦጋለ ፈለቀ የተጠቀሱት ችግሮች በመንግስት የተፈቱና እየተፈቱ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም መሰል ችግሮችን የመፍታቱ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

Advertisement