NEWS: በግብጽ የሰው አካል አዘዋዋሪ ዶክተሮች በቁጥጥር ስር ዋሉ::

                                                 

ግብጽ የሰው አካል በማዘዋወር ወንጀል የጠረጠረቻቸውን ዶክተሮች በቁጥጥር ስር ማዋሏን አስታወቀች።

እንደ ሃገሪቱ ፖሊስ ገለጻ ዶክተሮችን ጨምሮ ከህገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ጋር በመቀናጀት፥ የሰው ልጅ አካል በማዘዋወር የተጠረጠሩ በርካታ ሰዎች ተይዘዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም በመዲናዋ ካይሮ አቅራቢያ የሚገኝና ለዚህ ስራ ያገለግል የነበረን የህክምና ማዕከል መዝጋቱን ገልጿል።

የህክምና ማዕከሉ በተለይም የሰዎች ኩላሊት እየወጣ ለገበያ የሚዘጋጅበት ስፍራ ነበር ተብሏል።

የህክምና ባለሙያ የሆኑ ዶክተሮችም ኩላሊትን ጨምሮ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችን ከስደተኞች የማውጣቱን ስራ ይሰሩ ነበር ነው የተባለው።

ከስደተኞች የወጡት የሰውነት ክፍሎችም ሃብታም ግብጻውያንን ጨምሮ ለሌሎች የውጭ ሃገር ዜጎች እንዲሸጡ ይደረጋል።

ከሰባት አመት በፊት የአለም ጤና ድርጅት ግብጽ የሰው አካል እየወጣ ከሚዘዋወርባቸው ቀዳሚዎቹ ሃገራት ተርታ አንዷ ናት ማለቱን ተከትሎ፥ ይህን መሰሉ ተግባር በወንጀል ድርጊት መፈረጇ ይታወሳል።

ከወንጀሉ ጋር ተያይዞ ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ግን አልተገለጹም።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement