NEWS: በእናቶችና ህፃናት ጤና ላይ ያተኮረ ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀመረ

                                       

በደስታ ተካ

በእናቶች እና ህጻናት ጤና ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ መካሄድ ጀምሯል።

በኢትዮጵያ እና ሕንድ ትብብር የተዘጋጀውን ጉባኤ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ በንግግር ከፍተዋል።

በጉባኤው ሚንስትሮች፣ ከ24 ሃገራት የተውጣጡ ከመንግስት እና ከግሉ ዘርፍ የተውጣጡ ተወካዮችና የፖሊሲ አውጪዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

ጉባኤው በእናቶችና ህጻናት ጤና ላይ የተሰሩ ስራዎችን በማየት የተገኙ ምርጥ ተሞክሮዎችን ለማጋራት እና አፍሪካ በአውሮፓውያኑ የቀን አቆጣጠር 2030 ለመምታት ያስቀመጠቻቸውን የዘላቂ ልማት ግቦች ላይ ይወያያል ተብሎ ይጠበቃል።

ለሁለት ቀን የሚቆየው ጉባኤው በእናቶችና ህጻናት ጤና አጠባበቅ ላይ ባሉ መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች ላይ በመወያየት አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ነው የሚጠበቀው።

የኢፌዴሪ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃን ጉባኤውን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፥ ጉባኤው ኢትዮጵያ የእናቶችና ህፃናት ሞትን በመቀነስ ያስመዘገበችውን ውጤት ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳየት መልካም ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

Advertisement