NEWS: ጦጣዎች የሚያስተናግዱበት የጃፓን መጠጥ ቤት የቱሪስት መስህብ ሆኗል::

                                       

በጃፓን የሚገኝ አንድ መጠጥ ቤት ሲገቡ ከተለመደው ውጪ ጦጣዎች ሲያስተናድ ይመለከታሉ።

መጠጥ ቤቱ ባሉት ለየት ያሉ አስተናጋጆቹም የበርካቶችን ቀልብ ስቧል የተባለ ሲሆን፥ ቱሪስቶችም ይህንን ለመመልከት ወደ ስፍራ እየተጓዙ ነው ተብሏል።

በቅርቡ የተቀረፀ ቪዲዮ እንደሚያሳየውም በጃፓን ካያቡኪ መጠጥ ቤት ውስጥ ፉኩ ቻን የተባለ እና የ17 ዓመት እድሜ ያለው ጦጣ እየተዘዋወረ ሲያስተናግድ ያሳያል።

ፉኩ ቻን የተባለው ይህ ጦጣ መጠጥ ለመጎንጨት ጎራ ላሉ ሰዎች የተለያዩ አይነት መጠጦችን ሲያቀርብ እና የንፅህና መጠበቂያ ወረቀቶች (ናፕኪን) ሲያቀርብላቸውም ታይቷል።

የመጠጥ ቤቱ ባለቤት ካዎሩ ኦቱስካ፥ “ጦጣዎቹን ወደ ስራ ቦታ ይዣቸው እመጣ ነበር፤ በድንገት ያቻን የተባለው ጦጣ ለደንበኞች የንፅህና መጠበቂያ ወረቀት (ናፕኪን) ሲያቀብል አየው” ይላል።

ፉኩ ቻን የተባለው ሌላኛው ጦጣም ያቻንን በመከተል ሰዎችን እያስተናገደ ነው ሲልም ተናግሯል።

የመጠጥ ቤቱ ባለቤት በአሁኑ ጊዜ በርካታ ትናንሽ ጦጣዎች ያሉት ሲሆን፥ ጦጣዎቹም ወደ መጠጥ ቤቱ ጎራ ካሉ ሰዎች ጋር ፎቶ ለመነሳት እንጂ ለመስተንግዶ አልበቁም ተብሏል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement