NEWS: የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ለሁለት ምሁራን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጠ::

                                           

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ቦርድ ለሁለት ምሁራን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጠ።

ቦርዱ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ የሰጠው ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ክንደያ ገብረህይወትና በዩኒቨርሲቲው የባይሎጂ ትምህርት ክፍል ባልደረባ ለሆኑት ዶክተር ግደይ ይርጋ ነው።

ለሁለቱ ምሁራን የፕሮፌሰርነት ማዕረጉ የተሰጠው በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በርካታ የምርምር ስራዎችን ለህትመት በማብቃታቸውና በማስተማር ስራቸው የላቀ ውጤት ማስመዝገባቸው በመረጋገጡ ነው።

የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ክንደያ ገብረ ህይወት ለሙሉ የፕሮፌስርነት ማእረግ የበቁት በዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች ተመድበው ውጤታማ ስራ ከማከናወን ባለፈ ተጨባጭ የምርምርና የአካዳሚክ ስራዎችን አከናውነዋል።

ምሁሩ የሁለተኛና የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን በማማከር ለሃገራችን የከፍተኛ ትምህርት እድገት ካበረከቱት አስተዋጽኦ ባለፈ በምርምር ስራዎቻቸውና በላቀ የአመራር ክህሎታቸው በበርካታ ተቋማት እውቅና የተቸራቸው እንደሆኑም ዩኒቨርሲቲው ያወጣው መግለጫ አመልክቷል።

በዚህም እንደ አውሮፓያኑ አቆጣጠር በ2004 ለተመራማሪዎች የሚበረከተው “የተቀናጀ የልማት ዓለም አቀፍ ሽልማት”፣ በ2005 ደግሞ በአፍሪካ በትምህርት ልማት ዘርፍ የላቀ አመራር ላበረከቱ ምሁራን የሚሰጠውን የአመራር ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል።

ሌላኛው የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ የተሰጣቸው ዶክተር ግደይ ይርጋ ደግሞ ከኒውዚላንድ ለይደን ዩኒቨርሲቲና ከቤልጂዬም አንትወርፕ ዩኒቨርሲቲ ሁለት የዶክትሬት ትምህርቶችን በአንዴ የተቀዳጁ ብቸኛ ምሁር ናቸው።

ዶክተር ግደይ በ2014 ላይ ምርጥ ተመራማሪ በመባል ተሸላሚ ሲሆኑ፥ በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የምርምር ስራዎች ላይ በመሳተፍ ውጤታማ መሆናቸውም ተመልክቷል።

በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸውም በማስተማርና በምርምር ስራቸው ውጤታማ ምሁር መሆናቸው በመረጋገጡ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማእረግ ተሰጥቷቸዋል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement