NEWS: በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክ አቀባበል ተደረገለት::

                                   

በለንደን አስተናጋጅነት በተካሄደው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ጠዋት ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

በአቀባበል ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ርስቱ ይርዳው በለንደን አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተገኘው ውጤት የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ ሜዳሊያ ያሸነፉና በውድድሩ ተሳትፈው የተመለሱ አትሌቶችን አበረታተዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ በበኩሉ፥ በ16ኛው ሻምፒዮና ተፎካካሪዎቻችን ያሉበትን ደረጃ የተመለከትንበትና ጠንክረን እንድንሰራ የሚያደርግ ነው ብሏል፡፡

ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው 2 የወርቅ እና 3 የብር በአጠቃላይ 5 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከዓለም ሰባተኛ ከአፍሪካ ደግሞ ሶስተኛ ሆና አጠናቃለች፡፡

አልማዝ አያና በ10 ሺህ ሜትር እንዲሁም ሙክታር ኢድሪስ በወንዶች 5 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያዎችን አስገኝተዋል፡፡

የብር ሜዳሊያዎችን ደግሞ ጥሩነሽ ዲባባ በ10 ሺህ ሜትር፣ አልማዝ አያና በ5 ሺህ ሜትር እና ታምራት ቶላ በማራቶን ለኢትዮጵያ አምጥተዋል፡፡

ከሁለት ቀን በፊት ፍጻሜውን ባገኘው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አሜሪካ 10 የወርቅ፣ 11 የብር እና 9 የነሃስ ሜዳሊያዎች በድምሩ 30 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ አንደኛ ሆና አጠናቃለች።

ኬንያ 5 የወርቅ፣ 2 የብር እና 4 የነሃስ በድምሩ 11 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከዓለም ሁለተኛ ከአፍሪካ አንደኛ ሆና ጨርሳለች፡፡

ደቡብ አፍሪካ 3 የወርቅ፣ 1 የብር እና 2 የነሃስ በድምሩ 6 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ከዓለም ሶስተኛ ከአፍሪካ ደግሞ 2ኛ በመሆን ሻምፒዮናውን ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡

ፈረንሳይ በ3 የወርቅ እና 1 የነሃስ ሜዳሊያ 4ኛ፣ ቻይና በ2 ወርቅ፣ 3 ብር እና 2 ነሃስ በድምሩ በ7 ሜዳሊያዎች 5ኛ ደረጃን ሲይዙ፥ አዘጋጇ እንግሊዝ በ2 ወርቅ፣ 3 ብር እና 1 ነሃስ 6ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን አጠናቃለች።

ከሀምሌ 28 እስከ ነሃሴ 7 2009 ዓ.ም በለንደን አስተናጋጅነት ለ10 ቀናት በተካሄደው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 43 ሀገራት የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ መግባት ችለዋል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement