ሲያስመልስዎት መወሰድ ያለባቸው የመፍትሄ እርምጃዎች::

                                              

ማስመለስ በጤና መታወክም ይሁን በሌላ ምክንያት ሊከሰት የሚችል የጤና ችግር ነው።

የምግብ አለመስማማት፣ የምግብ መመረዝ፣ አዕምሮ ላይ የሚከሰት ጉዳት፣ ከልክ በላይ መመገብ፣ እርግዝና፣ የመድሃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት፣ ከልክ በላይ አልኮል መጠጣት ለዚህ ችግር ይዳርጋሉ።

ይህ ችግር ሲከሰት ደግሞ ከህክምና በፊት በራስ አቅም መወሰድ የሚገባቸው የመፍትሄ እርምጃዎች ይኖራሉ።

በጥልቅ መተንፈስ፦ በጣም አየር ወደ ውስጥ እየሳቡ በአፍንጫ በጥልቅ መተንፈስ ሲያስመልስዎ የመኮማተር አይነት ስሜት ላይ የነበረውን ሆድ የተሻለ የመለጠጥ አቅም እንዲያገኝ ይረዳዋል።

ይህንን በመደጋገምም የሆድ አካባቢ መጨናነቅና መኮማተርን በማስወገድ ነጻ የሆነ ስሜት እንዲሰማው ማደረግ ይቻላል።

ከመዳፍ በታች ባለው የእጅ አንጓ ላይ የደም ስር አካባቢ ያለበትን ቦታ ጫን በማለት መያዝም ለዚህ መፈትሄ እንደሆነ የቻይና ባህላዊ ህክምና አዋቂዎችን ዋቢ ያደረጉ መረጃዎች ያሳያሉ።

ለዚህ ሶስት ጣትን በዚህ ክፍል ላይ በማስቀመጥ እና አውራ ጣትን በማስደገፍ እስከ ሶስት ደቂቃ ድረስ በማሸት ይህን ችግር ማስቆም ይቻላል።

ይህን ማድረጉ ለደቂቃዎች የተስተጓገለውን የደም ዝውውር ስርዓት ለማስተካከልም ይረዳል።

ዝንጅብልና ቅርፉንድ፦ ይህን በሻይ መልክ በማፍላት መጠቀምም ለዚህ ችግር ሌላው መፍትሄ ነው።

ይህ ደግሞ በተለይም በእርግዝና ወቅትና በህክምና ወቅት ለሚከሰት የማስመለስ ችግር መፍትሄ መሆኑም ይነገራል።

ከ5 እስከ 10 ደቂቃ ከሻይ ጋር በማፍላት ዝንጅብሉን መጠቀም፥ እንዲሁም ቅርፉንዱን ከሻይ ጋር በጥቂቱ በማፍላትና በመጠቀም በመፍትሄነት መጠቀም ይቻላል።

ቅርንፉድ በውስጡ በያዘው ፀረ ባክቴሪያ ንጥረ ነገር አማካኝነት ይህን ችግር ለመቅረፍ ተመራጩ ነው።

ውሃ መጠጣት፦ ካስመለሰዎት በኋላ አረፍ እያሉ በጥቂቱ ውሃ በብዛት መጠጣት ይኖርብዎታል።

ከዚህ ባለፈም እንደ አረንጓዴ ሻይ ያሉ መጠጦን አፍልቶ መጠቀምም ይመከራል።

ሎሚ መምጠጥም ከውሃ በኋላ ቢያደርጉት ይመከራል።

ከዚህ ባለፈም የሜንት ቃና ያላቸውን ከረሜላዎች መጠቀምም በዚህ ወቅት ከዚያ ስሜት ለመውጣት ይረዳል።

በቂ እረፍት ማድረግም ሰውነት ያጣውን ጉልበት እንዲያገኝ ይረዳዋል።

ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ወደ መድሃኒት ቤት በማምራት ቫይታሚን ቢ6 መግዛትና መጠቀም ቢችሉ መልካም ይሆናል።

ይህ ምናልባት ማታ አልኮል በማብዛትዎ ምክንያት ካስመለሰዎት ያለውን የራስ ምታትና የመደንዘዝ ስሜት ለመቀነስ ይረዳል።

ከዚህ በኋላም ቀለል ያለ ምግብ በጥቂቱ በመመገብ ሻይ ነገር መጠጣት ይመከራል።

ምግብ ለመመገብ ግን እስከ 30 ደቂቃ መጠበቅና እስከዚያው ንጹህ ውሃ መጎንጨትና አረፍ ማለት።

ከዚያ በፊት የሚወሰድ ምግብ በድጋሚ እንዲያስመልሱ ሊያደርግ ስለሚችል መውሰዱ አይመከርም፤ በተደጋጋሚ ማስመለስ ጨጓራን ለጉዳት ይዳርጋልና።

ማስመለሱ ተደጋጋሚና የበዛ ከሆነ ደግሞ ሃኪም ዘንድ ጎራ ማለት ይኖርበዎታል።

ማስመለሱ ከሳምንት በላይ የቆየ ከሆነ፣ ለእርጉዝ ሴቶች፣ ቤት ውስጥ የሞከሩት መንገድ መፍትሄ ካልሆነ፣ ከፍተኛ የሆነ የፈሳሽ እጥረት ሲከሰትና የተለየ ቀለም ያለው ፈሳሽ ከወጣ ወደ ሃኪም መሄድ ይኖርብዎታል።

ችግሩ ህጻናት ላይ ከሆነ ግን የተመገቡትን ነገር መጠየቅና ማወቅ በተቻለ ፍጥነትም ወደ ህክምና ተቋም ማምራት አስፈላጊ ነው።

ምንጭ:- ጤናችን

Advertisement