በግሩም ተበጀ
የዛሬ 2ሺ ዓመታት ግድም የነበሩት ጥንታዊያን ግሪኮች፣ በወቅቱ የነበሩትን አስደናቂ የሰው ልጅ የፈጠራ ውጤቶችን በዘረዘሩበት የ7ቱ የዓለማችን አስደናቂ ነገሮች ዝርዝር ውስጥ ያለው ተንጠልጣዩ የባቢሎን አጸድ (The Hanging Garden of Babylon)፣ የፍቅር መታሰቢያ፣ የመውደድ ገጸ በረከት ነው ማለት ይቻላል፡፡
የባቢሎኑ ንጉሰ ነገስት ናቡከደነጾር ሁለተኛ፣ “ሀገሬ ናፈቀኝ፣ የሀገሬ ዛፎች፣ የአበቦቹ መዓዛ፣ ትውስታው በአይኔ እየመጣ ናፍቆቱን አልቻልኩትም” እያለች ላስቸገረችው ተወዳጅቱ ንግስት፣ የአባቷን ግዛት ሜዲያን ሲያስገብር በምርኮ አምጥቶ ላገባት ለሜዲያዋ አሚታስ የአይን ረሀብ ማስታገሻ የተገነባ ነበር፡፡
የሀገሯ ዛፎችና ዕጽዋት የተተከሉበት ከመሬት ከፍ ብሎ ማማ ላይ የተገነባው ግዙፉ አጸድ ከዘመኑ አስደናቂ ነገሮች አንዱ ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ያ አስደናቂ አጸድ የለም፡፡ ገና ድሮ፣ ያኔ በጥንቱ ዘመን ነበር የወደመው፡፡ ዛሬ ላይ የት እንደነበርም ቦታው በውል አይታወቅም፡፡
የጊዜ አብራክ የሚወልዳቸው፣ የተፈጥሮ አደጋው፣ መሬት መንቀጥቀጡና ሌላ ሌላውም ተደማምረው በጊዜ አሟሚ መዳፍ ውስጥ በንነው ጠፍተዋል፡፡ ከአንዱ ቋንቋ ወደ ሌላው ሲተረጎሙ ዛሬ ላይ የደረሱ መዛግብት ብቻ ናቸው የዚህን የፍቅር ገጸበረከት (ተንጠልጣይ አጸድ)ና የሌሎቹንም አስደናቂ ነገሮች ትውስታ ጠብቀው ተከታታይ ትውልዶች አሁንም ድረስ የሚያነሳሷቸው፡፡
በርግጥ ከአንዱ በስተቀር ነው ታዲያ
ከአንዱ በስተቀር!
ፒራምድን ሰይጨምር…
ጥንታዊው የአረብ ተረት ስራው ጊዜን ይፈጥራል፣ ጊዜ ደግሞ ፒራሚድን እያለ የሚያሞካሻቸውን የግብጹን የጊዛን ታላቁን ፒራሚድ ሳይጨምር ነው ታዲያ፡፡
ባለቅኔው የጊዜ ጉንጭ ላይ እንባ ሲል ስለተቀኘላት የዓለማችን እጅግ ውብ የፍቅር መታሰቢያ – ስለ ታጅ ማኻል !!
በነጭ እምነበረድ ታንጾ ለዘመናት የዘላለማዊ ፍቅር ተምሳሌት ሆኖ የዘለቀው የውቢቷ የሙንታዝ ማኻል ዘላለማዊ ማረፊያ ስለሆነው ስለ ታጅ ማኻል እና ከአስደማሚው ውብ ህንጻ ጀርባ ስላለው የሻህ ጅኻንና የሙንታዝ ማኻል የፍቅር ታሪክ ነው፡፡
…
ፍቅር መጀመሪያ አለው ከተባለ፣ ታሪኩ የተጀመረው እ.አ.አ በ1607 መላውን ህንድ የሚያስተዳድረው የሞጉሉ ኢምፓየር ንጉሰ ነገስት ተወዳጅ ልጅ፣ የ15 ዓመቱ ልዑል ኩህራም፣ በቤተ መንግስቱ አጀብ ተከቦ ወደ ሚና ባዛር (ገበያ) ብቅ ባለበት ዕለት ነው፡፡
የታዳጊው ልዑል አይኖች በሃር አልባሳትና ጌጣጌጦች የተዋበችው ፐርሺያዊቷ ልዕልት አርጁማንድ ባኑ ቤጉም ላይ አረፈ። የአይን ፍቅር በሉት፤ ብቻ አንዴ እንዳያት ነበር የወደዳት፡፡
በእሷ በኩል ያለውን አናውቅም። ልዑል ኩህራም ግን ወዲያውኑ ነበር ስለዛች የለጋ ወጣት ልቡን ስለሰለበችው ኮረዳ ለንጉስ ነገስት አባቱ የተነፈሰው። ያኔ ልዑሉ የ15፣ ልዕልቲቱ ደግሞ የ16 ዓመት ኮረዳ ነበረች፡፡ በወቅቱ፣ በሌሎች ዓለማት የነገስታት ታሪኮች ውስጥ እንደሚታየውና፣ በሀገራችን የነገስታት የፖለቲካ ታሪክ ውስጥም በስፋት እንደሚስተዋለው ልዑላን ለፍቅር ብቻ አያገቡም፡፡
ስለወደዱ ብቻ፣ ልብ ስለከጀለ፣ መውደድ ነፍስን አነሁልሎ፣ ፍቅር በልብ ስላጎነቆለ፣ መንፈስ በፍቅር ስለጦዘ ብቻ የወደዱትን ማገባት – ባብዛኛው አይታሰብም፡፡ ልዑላንም ሆኑ ነገስታት ራሳቸውም ጭምር፣ ለፖለቲካዊ ጥቅም ሲባል፣ እንደ ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳ ፖለቲካዊ ጋብቻን ማካሄድ በስፋት የተለመደ ቤተመንግስታዊ የትዳር ስልት ነው፡፡
ከዚህ ውጪ ግን የሞጉል ነገስታትም ሆኑ ልዑላኖች የቻሉትን ያህል ዕቁባቶች ቢኖሯቸው ስነ መንግስታዊ መብታቸው ነው፡፡ እናም፣ ምንም እንኳ የልዑል ኩህራም የወጣት ልብ በፍቅር ቢከንፍ፣ ፖለቲካዊ ፋይዳውም ከግምት ውስጥ ገብቶ፣ በልደት ቀኑ በወርቅና በከበሩ ድንጋዮች እንደተንቆጠቆጠ፣ ልቡን ያማለለችው ፐርሺያዊቷ ጉብል ታጨችለት፡፡
በዕርግጥ ይህ ፍቅር ከታቀደለት ፖለቲካዊ ፋይዳ አልፎ – ዘላለማዊ ለመሆን በቃ፡፡
ሞጉሎች ኃይለኛ ተዋጊዎች ናቸው። ስረ መሰረታቸው ከታዋቂው የሞንጎሎች መሪ ጂንጂስካን ይነሳል፡፡ የሞንጎል ወራሪ ጦር ከዚህ ታሪካዊ ወቅት ወደ ኋላ ባሉት ጥቂት መቶ ዓመታቶች ውስጥ፤ በክፍለ ዓለሙ ለነበሩ ሰልጣኔዎችና ህዝቦች አስደንጋጭ የቀን ቅዠት ነበር፡፡ በነበሩበት ቦታና ዘመን፣ ያላወደሙት ስልጣኔና ያልጨፈጨፉት ህዝብ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ራቅ ባለው ዘመንማ ቻይና ራሷ የእነሱን ወረራ ለመመከት ነበር በዝነኛው የቻይና ግንብ ግዛቷን ያጠረችው፡፡
ከዚህ ታሪካዊ ወቅት አንድ መቶ ዓመታት ወደኋላ ባለው ጊዜም ከሰሜናዊ ህንድ በመነሳት አንዱን የህንድ ከተማ ሲቀጥል ሌላውን እየደረማመሱ በ2000 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ መላዋን ህንድ በአንድ ግዙፍ ግዛት ስር ለማስተዳደር በቁ።
ቀስ በቀስም ሞንጎሎች የሚያስገብሯቸው ስልጣኔዎችና ህዝቦች ኃይማኖትና ባህል እየተዋሃዳቸው መጣ። እናም በዚህ ታሪካዊ ወቅት ሞጉሎች ስልጡን የግዙፉ የህንድ ግዛት አስተዳዳሪዎች ሆነዋል፡፡ ኃይማኖታቸው እስልምና ነው፡፡ የብዙሀኑን የሂንዱ ዕምነት አክብረው፣ የሀይማኖት መቻቻልን እየሰበኩ፣ በግዛቱ ውስጥ ላለው ከ100 ሚሊዮን በላይ ለሚሆን ህዝብ ንግድና ኢንደስትሪው፣ ሳይንስና ኪነጥበቡ ሰምሮለታል፡፡ ባጠቃላይ ሞጉሎች የተዋጣላቸው ስልጡን አስተዳዳሪዎች ሆነዋል፡፡
የጦር ስልት አዋቂነታቸውና የሀይለኛ ተዋጊነታቸውንም የዘር ውርስ ሳይዘነጉ ነው ታዲያ…
ለዚህም ነው፣ እ.አ.አ በ1617፣ የ25 ዓመቱ ልዑል ኩህራም የግዛቲቱን አማጽያንና ጠላቶቹን አንድ በአንድ ደመሰሰ፡፡ ወጣቱ ልዑል በስኬት ላይ ስኬት በድል ላይ ድል ደረበ፡፡
እንዲሁም የንጉስነገስት አባቱ ተወዳጅ ልጅ የሆነው ልዑል ኩህራም፣ ይህ አንጸባራቂ ድል ሲታከልበት፣ ንጉሰነገስት አባቱ ሻህ ጅኻን (የአለም ንጉስ) የሚል የማዕረግ ስም አጎናጸፈው፡፡ ለአንድ ገና ላልነገሰ ልዑል እንዲህ ያለ የማዕረግ ስም መስጠት ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ የነገውን ብሩሁን የንጉስ ነገስትነት ተስፋ ያመላክታል፡፡
በዚህ ሁሉ ጊዜ ውስጥ ደግሞ የልቡ ንግስትና ከሌሎች ሁሉ አስበልጦ የሚወዳት የቤተ መንግስቷ ምርጥ(The Chosen One of the Palace) ‘ሙንታዝ ማኻል’ ሲል የሚጠራት የልጅነት ፍቅሩ አብራው አለች፡፡
ምንም እንኳ ሻህ ጅኻን ሌሎች በርካታ ዕቁባቶች ቢኖሩትም፣ የምንጊዜም ተወዳጁ የልጅነት ፍቅሩ ሙንታዝ ማኻል ነበረች፡፡ በተገኘው ጊዜ ሁሉ አብረው ናቸው፤ ተነጣጥለው አያውቁም።
የቤተ መንግስት ዜና መዋዕል ጸሀፊዎች በሁለቱ መሃል የነበረውን ቅርርብ፣ ተጣጥሞሽና ፍቅር እንዲህ ሲሉ ይገልጹታል፣ “በመካከላቸው የነበረው መዋደድና ተጣጥሞሽ (Harmony) ከዛሬ በፊት በነበሩት በየትኛውም ሀገራት ልዑላን ጥንዶች መካከል ከነበረው እጅጉን የላቀና፤ ሻህ ጅኻን ለሙንታዝ ማኻል ያለው ፍቅርና መሰጠት ለሌሎች ካለው መውደድ አንጻር በሺዎች እጥፍ ይበልጣል…”
እ.አ.አ በ1621፣ የሻህ ጅኻን አባት ንጉሰ ነገስቱ ታመሙ፡፡ ልጆቹ ተሰባስበዋል፡፡ ከአባትዬው ህልፈት በኋላ፣ የንጉሰ ነገስቱን ስልጣን ለመያዝ በልዑላኑ መሃል የሰልጣን ሽኩቻው ተጀመረ፡፡
ሻህ ጅኻን በተገኘው ስልት ተጠቅሞ የስልጣን ተቀናቃኞቹን አስወገደ፡፡ እናም ከሰባት ዓመታት በኋላ እ.አ.አ በ1628 በሞጉል ኢምፓየር ዋና ከተማ በሰሜናዊ ህንዷ አግራ ላይ ቀድሞ አባቱ ያጎናጸፉትን ሻህ ጅኻን የሚለውን ማዕረጉን እንደተጎናጸፈ የንጉሰ ነገስትነቱን ዘውድ ደፋ፡፡
ሻህ ጅኻን በጦር ሜዳ ጀግንነት ብቻ ሳይሆን በአስተዳደሩም ብልህና የተመሰገነ ሆነ፡፡ ሰፊውን ግዛቱን በፍፁማዊ አስተዳደሩ ስር ወደ ብልጽግና መራት፡፡
ሞጉሎች እጅግ ሀብታም ነገስታት ናቸው። ህንድ ወደ ውጪ በምትልካቸው እንደ ወርቅ፣ የከበሩ ድንጋዮች፣ ቅመማ ቅመምና የአልባሳት ንግድ ከብረዋል፡፡
በዋና ከተማዋ አግራ ውስጥ ባለውና ቀዩ ምሽግ በሚሰኘው ሰፊ ቅጥር ውስጥ በሚገኙት ቤተ መንግስቶች ውስጥ ሻህ ጅኻንና አጠቃላዩ ንጉሳዊ ቤተሰብ የተንደላቀቀ የቅንጦት ህይወት ይመራሉ። የዚህ ሁሉ ፈርጥ ደግሞ ሻህ ጅኻን “የቤተ መንግስቷ ምርጥ” ሲል የሚጠራት የልቡ ንግስት ሙንታዝ ማኻል…፡፡ በወርቅና በአልማዝ ተንቆጥቁጣ፣ በፈርጥ በተሸመኑ አልባሳት ተውባ፣ በተዋቡ ደንገጡሮቿ ታጅባ ስትታይ፣ “…ጨረቃ እንኳ በውበቷ አፍራ ፊቷን ትሸፍናለች” ሲሉ ባለቅኔዎች የተቀኙላት ሙንታዝ ማኻል…!
በዚህ ሁሉ መሃል ግን በአንዳንድ ራቅ ባሉ የንጉሰ ነገስቱ ግዛቶች ውስጥ ብጥብጥና አመጽ ተቀጣጥሏል፡፡ አመጹን ለመቆጣጠር ደግሞ ንጉሰ ነገስቱ ግዙፉን ሰራዊቱን አንቀሳቅሶ በክተት ዘመተ፡፡
በደስታም ሆነ በሀዘን፣ በየትኛውም ሁነት ውስጥ የልቡ ልዕልትና አማካሪው ጭምር የሆነችው፣ በእልፍኝም ሆነ በዘመቻ ከጎኑ የማትለየው ሙንታዝ ማኻልም ለሁለት አመታት በዘለቀው በዚህ ዘመቻ አብራው ተጉዛለች። በተለይም ዴካን በተባለው ግዛት በተደጋጋሚ የሚነሳውን አመጽ ለማጥፋት በተደጋጋሚ ከቤተ መንግስቱ እየተነሳ ሲዘምት ከጎኑ አልተለየችም፡፡ አንዱ አመጽ ሲበርድ ሌላው እየጋመ ሻህ ጅኻንና የልቡ ንግስት ሙንታዝ ማኻል ከግዙፉ ሰራዊትጋ በዘመቻ ተንጠራወዙ፡፡
በዚህ አስቸጋሪ የዘመቻ ወቅትም ነበር ሻህ ጅኻን ሊቋቋመው ያልቻለው ሀዘን የወረደበት፡፡ በዚህ አስቸጋሪ የዘመቻ ወቅት፤ ሙንታዝ ማኻል የንጉስ ነገስቱን 19ኛ ልጅ አርግዛለች፡፡ እናም 19ኛ ልጇን ከተገላገለች በኋላ ወሊዱን ተከትሎ የተከሰተው የጤና ዕክል የአራሷን ሙንታዝ ማኻል ህይወት አስለመለመው፡፡
በጦር ሜዳ ጠላቶቹን አንድ በአንድ ሲጥል የነበረው የአለም ንጉስ ሻህ ጅኻን፣ የግዙፉ የሞጉል ኢምፓየር ገዢ፣ በሀብት የናጠጠው ንጉሰ ነገስት ሻህ ጅኻን አሁን በዚህ ክፉ ዕጣ ፊት ምንም ጉልበት የለውም። እናም ያለው ብቸኛ አማራጭ ይኸው ነውና፤ ፊቱን ወደ አምላኩ መልሶ ጸለየ፡፡ ተለማመነ። አነባ። ግን አልሆነም፡፡
የሻህ ጅኻንን ዓለም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያንኮታኮተውን ክስተት ዜና መዋዕሉ እንዲህ ይገልጸዋል፣ “ሰኔ 17 ቀን፣ 1632 በጣሙን መራር የሆነው ክስተት ሆነ። የግርማዊነትዋ ንግስት በአራስ ቤት እንዳሉ ማረፍ መላውን ዓለም የሀዘን ቤት አደረገው፡፡ የሻህ ጅኻን ዓለም አከተመ፡፡ ሻህ ጅኻን ለ8 ቀናት ምግብ አልቀመሰም፡፡በትካዜ እንደተቆራመተ ከሰው ሳይገናኝ ለብቻው ተነጥሎ አዘነ፡፡ ለሁለት ዓመታት ምንም አይነት ሙዚቃ አላዳመጠም፡፡ ምንም አይነት ጌጣጌጥም ሆነ ሽቶም አልተቀባም፡፡ ጺሙና ጸጉሩ ባንዴ ሸበተ፡፡ ባንዴ አረጀ፡፡ ባንዴ በጣም በጣሙን ያረጀ ሰው መሰለ፡፡
ትውፊቶች እንደሚሉት ሙንታዝ ማኻል ከመሞቷ በፊት ከዚህ በፊት በዓለም ታይቶ የማይታወቅና እጅግ ውብ የሆነ የመታሰቢያ መቃብር እንዲያስገነባላት መናዘዟን ይገልጻሉ፡፡
የሆነው ሆኖ፣ ድንገት አለሙ የጨለመበት ሻህ ጅኻን፣ የተወዳጇን ንግስት፣ የሙንታዝ ማኻልን፣ የተዋበ የመታሰቢያ መቃብር ማስገንባት የቀሪ ህይወቱ ዋንኛው ግብ ሆነ፡፡
የንጉሰ ነገስቱ መንግስት ካዝና፣ የአጠቃላዩ ግዛት ሀብት፣ የትኛውም አለ የተባለ የምህንድስና ሊቅ፣ በግምባታ የተካነው፣ በማስዋብ ከሁሉም የላቀው ባለሙያ ሁሉ ከመላው የሀገሪቱ ግዛት ተሰበሰበ፡፡ አሁን የንጉሰነገስቱ ዋንኛውና ቀዳሚው ግብ፣ የሙንታዝ ማኻል ዘላለማዊ ማረፊያ የሚሆነው፣ በውበቱ ተወዳዳሪ የለሹ ውብ የመታሰቢያ መቃብር ይሆናል – ታጅ ማኻል !
ግንባታው፣ ሙንታዝ ማኻል ከሞተች ከ6 ወራት በኋላ ተጀመረ፡፡ የግንባታው ቦታ ከመላው ግዛት በተሰበሰቡ ምርጥ ባለሙያዎች፣ የግንባታ ዕቃ በሚያመላልሱ ዝሆኖች ተሞላ፡፡ ለግንባታው የተመረጠው የያሙና ወንዝ ዳርቻ መሆኑ፣ የግንባታውን ግዙፍ ክብደት ከመሸከም አንጻር እክል ፈጠረ፡፡
በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በመጠኑ ለየትም ብሎ ቢሆን ጥቅም ላይ የሚውለውንና ፣ለዛን ዘመን ግን እጅግ ወጥ የሆነውን አዲስ ዘዴ ለመጠቀም ተገደዋል፡፡ በግንባታው ቦታ በርካታ ጥልቅ ጉድጓዶች በመቆፈር፣ በድንጋይና በሞርታር ሞሉት፡፡
ከዛም በላዩ ላይ ግዙፍ የድንጋይ ቋሚዎች በማቆም፣ በቅስት ግንባታዎች አያያዟቸው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ የታጅ ማኻልን ሙሉ ግንባታ መሸከም የሚችለው የድንጋይ የመሰረት ንጣፍ ተጣለ፡፡
የታጅ ማኻል ግንባታ ከፍተኛ ክህሎት በታከለበት ፍጥነት ይጣደፍ ጀመር፡፡ መላው ግንባታ እቦታው ላይ በገፍ በተመረተ ሸክላ ተገንብቶ ሲያበቃ፣ መላው የታጅ ማኻል ህንጻ ከ400 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በዝሆኖች ተጓጉዞ በመጣ እንከን የለሽ ነጭ እምነበረድ ተጌጠ፡፡
ሞጎሎች የተዋቡ የመታሰቢያ የመቃብር ህንጻዎችን ማስገንባት አዲሳቸው አይደለም፡፡ የራሱ ሻህ ጅኻን አባትም ሆነ ሌሎች ቀደምት የሞጉል ታላላቅ ነገስታት፤ የተዋቡ የመታሰቢያ የመቃብር ህንጻዎች ታንጸውላቸዋል፡፡
ይህ የሙንታዝ ማኽል ዘላለማዊ ማረፊያ ግን ከነዚህ ሁሉ ቀደምት ግንባታዎች በውበቱ የላቀ መሆን አለበት፡፡ እናም፣ የሻህ ጅኻን መሀንዲሶች ከዚህ በፊቶቹ ህንጻዎች የተለያዩ ማራኪና አብይ ገጽታዎችን በማዋሃድ እንደ ብዙዎች ግምት እስከዛሬ በሰው ልጅ ታልመው ከታነጹ ውብ ህንጻዎች ሁሉ ተወዳዳሪ የለሹን – ታጅ ማኻልን ያንጹት ጀመር፡፡
ዋናውን ህንጻ የከበቡትን አራት የሚናሬት ማማዎችን ከሻህ ጅኻን አባት የመታሰቢያ መቃብር ህንጻ ወስደዋል፡፡ የታጅ ማኻል ጉልህ መለያ የሆነውንና መሃንዲሶች አሁን ድረስ የሚደመሙበትን 40 ሜትር ከፍታ ያለውን ጉልላት ደግሞ ከሌላ ቀደምት የሞጉል ስመ ጥር ሰው የመታሰቢያ መቃብር ነው የወሰዱት፡፡
እነዚህን ሁሉ በማዋሃድና ልዩ ስነ-ውበታዊ ተጣጥሞሹን (Harmony) እንደጠበቀ፣ 20,000 ምርጥ ባለሙያዎች፣ ለ12 ዓመታት ተጠበውበት፣ በስተመጨረሻ፣ እ.አ.አ በ1643፣ ታጅ ማኻል፣ የሙንታዝ ማኻል ዘላለማዊ ማረፊያ፣ ስራው ተጠናቀቀ፡፡
ባለቅኔው፣ “የጊዜ ጉንጭ ላይ እንባ…” ሲል በተቀኘለት በዚህ ውብ ህንጻ እጅግ የተዋበው ውስጣዊው ክፍል ውስጥ፣ በስተመጨረሻ፣ የሙንታዝ ማኻል አስክሬን አረፈ፡፡ የታጅ ማኻል ተጓዳኝ የሆኑ ሌሎች ግንባታዎችም ለቀጣይ 10 ዓመታት ያህል ዘለቁ፡፡
በየዓመቱ፣ ሙንታዝ ማኻል ያረፈችበት ቀን ሲከበር፣ ሻህ ጅኻን የያሙናን ወንዝ በታንኳ እያቋረጠ ወደ ውዲቷ ንግስት፣ ሙንታዝ ማኻል፣ ዘላለማዊ ማረፊያ ያቀናል፡፡ ወደ ታጅ ማኻል፡፡ በየዓመቱ፡፡
የታጅ ማኻል ግንባታ የንጉሰ ነገስቱን ካዝና አሟጧል፡፡ በዚህም ላይ በህዝቡ ላይ የደረሰው ጫና ይህ ነው የሚባል አልነበረም፡፡ እንዲሁም በቤተ መንግስቱ የቅንጦት የኑሮ ዘይቤ ሳቢያ የተረቆሸው የሻህ ጅኻን መንግስት፣ ይህ እጅግ ውዱ የታጅ ማኻል ህንጻ ግንባታ ሲታከልበት፣ የሻህ ጅኻንን መንግስት አቅም ከዳው፡፡
እናም፣ እ.አ.አ በ1658፣ አንዳች ነገር ማድረግ እንዳለበት የተሰማው የራሱ ሻህ ጅኻንና የሙንታዝ ማኻል ልጅ፣ ከ30 ዓመታት የንጉሰ ነገስትነት ቆይታ በኋላ፣ በስተመጨረሻ ሻህ ጅኻንን ከስልጣን አወረደው፡፡
ከዚህ በኋላ ሻህ ጅኻን እስረኛ ነው፡፡ ህይወቱ እስካለፈችበት ጊዜ ድረስም ከታሰረበት የቤተ መንግስቱ የእስር ክፍል ውስጥ ሳይወጣ በእስረኝነት ተከርችሞበት ኖረ፡፡
ምሽት ላይ፣ የዜና መዋዕሉ ጸሃፊ፣ የያኔውን የወጣትነት ዘመኑን፣የጀብዱና በድል የተንቆጠቆጡ የጀግንነት ታሪኮቹን ያነብለታል፡፡ ብቸኛ መጽናኛው ግን ይሄ አልነበረም፡፡
ይልቅስ፣ በእስር ክፍሉ መስኮት አሻግረው ሲያዩ፣ ከያሙና ወንዝ ማዶ ነጭ የእምነበረድ እንክብል መስሎ የሚታየው፣ ሬቤንድራዝ ታጎር “የጊዜ ጉንጭ ላይ እንባ…” ሲል የተቀኘለት፣ የልጅነት ፍቅሩ፣ የሙንታዝ ማኻል ዘላለማዊ ማረፊያ፣ ታጅ ማኻል ነበር የኋለኛ ዘመኑ የዘላለማዊ ፍቅሩ መጽናኛ፡፡
እ.አ.አ በ1666፣ በ74 ዓመቱ፣ በስተመጨረሻ፣ ሻህ ጅኻን አረፈ፡፡ አስክሬኑም ከያሙና ወንዝ ማዶ፣ በተዋበው የታጅ ማኻል ውስጣዊው ክፍል ውስጥ፣ ከዘላለማዊ ፍቅሩ፣ ሙንታዝ ማኻል መቃብር ጎን አረፈ፡፡
እናም…
ሆነ…
ተፈጸመ፡፡
ምንጭ:- የሸገር FM 102.1 ሬዲዮ