SPORT: የካፍ ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ ጉብኝት አደረጉ

                                      

የአፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽን (ካፍ) ፕሬዚዳንት አህመድ አህመድ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት አደረጉ።

ትናንት ምሽት አዲስ አበባ የገቡት ፕሬዚዳንቱ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ፣ የአደይ አበባ ስታዲየም ግንባታን እና የካፍ ማዕከልን ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝቱ ወቅትም የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ርስቱ ይርዳው እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ጁነዲን ባሻ እና የጅቡቲ እግር ኳር ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት እና የካፍ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሱሌይማን ሃሰን ዋቤሪ ተገኝተዋል፡፡

በበጉብኝቱ ወቅት በማዕከሉ ሜዳ በስልጠና ላይ የተገኙት የአሴጋ አካዳሚ ታዳጊዎች ከፕሬዚዳንቱ ጋር የመተዋወቅ እድልን አግንኝተዋል፡፡ 

አሴጋ አካዳሚ ከወራት በፊት በድንገት ከዚህ አለም በሞት በተለየው የቀድሞው የብሄራዊ ቡድን አጥቂ አሰግድ ተስፋዬ ስር ይተዳደር የነበረ አካዳሚ ነው፡፡

የ57 ዓመቱ ማዳጋስካራዊ በአዲስ አበባ እየተገነባ በሚገኘው የአደይ አበባ ስታዲየም በመገኘት የግንባታውን ሂደት የተመለከቱ ሲሆን ግንባታውን በሚያከናውነው የቻይና ኩባንያም ገለፃ ተደርጎላቸዋል፡፡ 

አህመድ አህመድ በቀኑ የመጨረሻ መርሃ ግብርም አያት አካባቢ ያለፉትን 14 አመታት ተገንብቶ መጠናቀቅ ያልቻለውን የካፍ ማዕከል ጎብኝተዋል፡፡

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement