NEWS: አሜሪካ ከፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት እንደምትወጣ ለመንግስታቱ ድርጅት አስታወቀች::

                                   

አሜሪካ ከፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት እንደምትወጣ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት በፅሁፍ አስታወቀች፡፡

የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለተመድ በላከው ማብራሪያ የፓሪሱ አየር ንብረት ለውጥ ስምምነት አሜሪካን የሚጎዳ በመሆኑ ለመውጣት ተገዳለች ብሏል፡፡

ዋሽንግተን ከማዕቀፉ ትግበራ ራሷን ብታገልም በቀጣይ የበካይ ጋዝ ልቀትን በመቀነስ እና ነዳጅን በቴክኖሎጂ ለመተካት በሚደረገው ጥረት ተሳትፎ እንደምታደርግ ነው የጠቆመው፡፡

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የፓሪሱ ስምምነት አሜሪካውያንን ስራ ስለሚያሳጣ፣ በታክስ ከፋዮቿ እና በነዳጅ እና ተፈጥሮ ጋዝ አምራች ፋብሪካዎች ላይ አሉታዊ ጫና ስለሚፈጥር ከማዕቀፉ ትግበራ እንደሚወጡ ባለፈው ሰኔ ወር መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በበኩሉ የአሜሪካ ውሳኔ የአየር ንብረት ለውጥ ለውጥን ለመግታት እና የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት አደጋ ውስጥ እንደከተተው ገልጿል፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋይትሀውስ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቀጣይ በአየር ንብረት ለውጥ ስምምነቶች ላይ ድርድር ሊያደርጉ እንደሚችሉም ፍንጭ ሰጥቷል፡፡

ለአብነትም የፓሪሱ ስምምነት ከአሜሪካ ፍላጎት እና ከነደጃ አምራች ኩባንያዎቿ ጋር በማይጣረስ መልኩ ከተዘጋጀ፥ ማዕቀፉን እንደገና ለመቀበል የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በሩ ክፍት መሆኑን ነው የገለጸው፡፡

ሚኒስቴሩ ለተመድ ባቀረበው ማብራሪያ መሰረት ዋሽንግተን ከ2015ቱ የፓሪስ የበካይ ጋዝ ልቀት ቅነሳ ስምምነት ትግበራ አባልነት ሙሉ ለሙሉ ልትወጣ የምትችለው በ2020 ህዳር ወር ነው ተብሏል፡፡

የመውጣት ድርድሩም በ2019 ህዳር ወር ሊጀመር እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡

የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ከቻይና ቀጥሎ በበካይ ጋዝ ልቀት ሁለተኛ የተቀመጠችው ሀገራቸው፥ በ2005 የነበረውን 28 በመቶ የልቀት መጠን በ2025 ወደ 26 በመቶ ዝቅ ለማድረግ እንደሚሰሩ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

የአሜሪካ አየር ንብረት ለውጥ አቋም ባላፈው ሰኔ ወር በጀርመን ሀምቡርግ በተካሄደው የቡድን 20 ሀገራት ስበስባ መከፋፈልን መፍጠሩ ይታወሳል፡፡

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement