NEWS: በመዲናዋ የመሰረታዊ ሸቀጦች የስርጭት ካርድ አሰራር ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ አልሆነም::

                                             

በምስክር ስናፍቅ

በአዲስ አበባ የመሰረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ የተዘረጋው የስርጭት ካርድ አሰራር ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ባለመሆኑ በሸማቹ ህብረተሰብ የሚነሱ ቅሬታዎችን አሁንም መፍታት አልተቻለም።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች በመንግስት ድጎማ የሚቀርቡ ሸቀጦችን ለማግኘት ሌሎች ተጨማሪ እቃዎችን እንድንገዛ እንዲሁም የሸማች ኩፖንና መታወቂያ እንድናቀርብ እንጠየቃለን ብለዋል።

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 በሚገኝ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ሱቅ የተገኙ ሸማቾች በስርዓቱ እየተስተናገዱ እንዳልሆነ፣ የሚፈልጉት ሸቀጥ አልቋል እንደሚባሉና ሌሎች ቅሬታዎችን ተናግረዋል፡፡

በሌሎች የከተማዋ አካባቢዎችም ሸማቾች በስርዓቱ የሚስተናገዱበት ሁኔታ ቢኖርም፥ ጥቂት የማይባሉ የህብረት ስራ ማህበራት ሱቆች ግን በርካታ ጥያቄዎች እንደሚነሳባቸው ጣቢያችን በቅኝቱ ተመልክቷል፡፡

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት፣ ሶስት እና አራት የሚገኙ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ሱቆች ተመሳሳይ ቅሬታ የተነሳባቸው ሲሆኑ፥ በአንዳንዶቹ ሱቆችም የሸማች አባልነት ካርድ ያልያዘ አናስተናግድም የሚሉ ማስተወቂያዎች ተለጥፈዋል።

ችግሩ አሁንም የቀጠለ ሲሆን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በበኩሉ ጥቆማው አልደረሰኝም የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ቢሮው ከጥቆማው ባለፈ በቀጥታ ተጠያቂውን በቀላሉ ለመለየት የሚያስችል አሰራር ባለመኖሩ በክትትል ውቅት ችግሮችን እንዳላገኘ ጠቅሷል፡፡

ከዚህ ውጭ የመሰረታዊ ሸቀጥ አባወራና እማወራን ከቸርቻሪ ሱቆች ጋር ለማስተሳሰር የተዘጋጀው የስርጭት ካርድ እንደ ዘላቂ መፍትሄ መቀመጡን አንስቷል፡፡

በምዝገባ የሚለየው ሸማችም ሆነ የካርዱ አይነት በግልጽ የሚታወቅ በመሆኑ፥ ለነጋዴውም ሆነ ለማህበራቱ ሱቆች ሸማቹን በኮታ ከፋፍሎ በቀጥታ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል ነው ተብሎ ነበር፡፡

አሰራሩ ካሳለፍነው ጥር ጀምሮ ተግባራዊ ቢደረግም ችግሩ ግን አሁንም እንዳልተፈታ የሚያሳዩ ቅሬታዎች እየተነሱ ነው፡፡

የአዲስ አበባ የንግድ ቢሮ የድህረ ፍቃድ ኢንስፔክሽንና ሬጉላቶሪ ዳይሬክተሩ አቶ ካሳሁን በየነ በአሰራሩ ላይ የታየው ጉድለት የአፈጻጸም ችግር ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡

ቢሮው ሙሉ ለሙሉ ስርዓቱን ዘርግቻለው ቢልም፥ አስተያየት ሰጪዎች ከተናገሩት ባሻገር ጣቢያችን ባደረገው ቅኝት ስርዓቱ ተግባራዊ ያልተደረገባቸው ሱቆችን መኖራቸውን አረጋግጧል።

ትግበራው ከተጀመረ አምስት ወር ያስቆጠረ በመሆኑ በተባለው ደረጃ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ያላደረጉትን በመለየት እንዲያስተካክሉ እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡

ቢሮው በተባለው ደረጃ ተግባራዊ የማያደርጉት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ጠቅሶ፥ ከሚያደርገው ክትትል በተጓዳኝ ሸማቹ በ8588 ነጻ የስልክ መስመርን ጨምሮ በአካል በመምጣት እንዲጠቁም ጥሪውን አቅርቧል፡፡

በከተማዋ በመንግስት ድጎማ የሚቀርቡ መሰረታዊ ሸቀጦች ከ570 በላይ ለሆኑ የህብረት ስራ ማህበራት ሱቆችና ለቸርቻሪ ነጋዴዎች ተከፋፍሎ ነው ሸማቹ ጋር እንዲደርስ የሚደረገው።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement