የልጆችን አዕምሯዊ ጤንነት ለማሻሻል ከወላጆች የሚጠበቁ 6 ነገሮች

                                                           

በርካታ ወላጆች የልጆቻቸውን አዕምሯዊ ጭንቀት ቢረዱም፥ የማረጋጋት እና የተፈጠረውን የመረበሽ ስሜት በማስወገድ ረገድ ችግሮች እንዳሉባቸው የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡
የእንግሊዝ የጤና ባለሙያዎችም የልጆችን የአዕምሮ ጤንነት ለማሻሻል ወይም ለመጠበቅ የሚከተሉትን ስድስት ነገሮች ተግባራዊ ማድረግ መልካም ነው ብለዋል።

1. ልጆች እንዲናገሩ መፍቀድ፣ የሚናገሩትን ማዳመጥ
ወላጆች ከልጆች ጋር ማውራታቸው፣ ልጆቻቸውም የሚሉትን ማዳመጣቸው የግድ ይላል።
ወላጆች ራሳቸው አብዝተው አስተያየቶችን ከመስጠት እና ብዙ ከመናገር ይልቅ ለልጆቻቸው ብዙውን ጊዜ በመስጠት የሚናገሩትን ማዳመጥ፣ ስለስሜታቸው ለማወቅ ያግዛል ተብሏል፡፡
ይህን ማድረጉ ከሚያስቡት ባሻገር በወቅቱ ምን ዓይነት አዕምሯዊ ሁኔታ ላይ እንዳሉ አውቆ፥ መፍትሔ ለመስጠትም አመቺ ነው፤ ከልጆች ጋር ማውራት በራሱ እንዲዝናኑ ስለሚፈቅድላቸው ለአዕምሯቸው ምቾትን ይፈጥራል፡፡
ወላጆች ስለ አዕምሮ ጤንነት ለልጆች ማውራት በሚፈልጉበት ጊዜም ፍላጎታቸውን ማጤን ተገቢ ነው።

2. ትዕግስተኛ መሆን
የልጆች የአዕምሮ ጤና የተረበሸ በሚመስላቸው ጊዜ ወላጆች ምንም ማድረግ የማይችሉ ያህል ይጨነቃሉ፤ ይፈራሉም፡፡
ሆኖም ልጆች ያጋጠማቸውን የጭንቀት ወይም የመረበሽ ምክንያት እንዲያቀርቡ ማድረግ፤ ለዚህ ደግሞ ጊዜ መስጠት እና መታገስ ተገቢ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ልጆች ስላጋጠማቸው ነገር በይሉኝታ ወይም በመሸነፍ ስሜት ቶሎ ላይናገሩ ይችላሉ፤ በዚህ ጊዜ ምንም እንኳ ለወላጅ ማድረግ ቢከብድም ከመጨነቅ ርቆ ትዕግስተኛ መሆን ለቀጣይ የመፍትሔ እርምጃ እንዲያሰላስሉ በር ይከፍታል፡፡
ልጆች ወደውና ፈቅደው እስኪናገሩ መጠበቅ እና እንዲናገሩ ማበራታትም ተገቢ ነው የተባለ ሲሆን፥ ምክር እና እርዳታ ሊሰጥ የሚችል ሌላ የቤተሰብ አካል ካለ ለዚያ ሰው ማወያየትም ተመራጭ መሆኑ በባለሙያዎቹ ተጠቅሷል።

3. ከልጆች ጋር አብሮ ማሳለፍ
በቀን ከቀን ኑሮ ውስጥ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር አብረው መቆየት የሚፈልጉትን ያህል ጊዜ ላያሳልፉ ይችላሉ።
ምክንያቱም ስራን እና ልጆችን መንከባከብን ሁለቱንም በአንድ ማስኬድ ስለማይችሉ ነው፤ ሥራ ላይ በሚያሳልፉበት ጊዜም የልጆች ደህንነት ጭንቀት ውስጥ ይከታቸዋል፡፡
በዚህም ምክንያት ለልጆቻቸው የአዕምሮ መረበሽ ተጠያቂ የመሆን እና ጥፋተኛነት ይሰማቸዋል፤ ይህ እንዳይሆን በተቻለ መጠን ጊዜን አመጣጥኖ ከልጆች ጋር ማሳለፍ ይመከራል፡፡
ስለሆነም የልጆችን የአዕምሮ ጤና ለማሳደግ እና ደስታቸውን ለመጨመር የሚያስችሉ የመወያያ እና የመዝናኛ ጊዜን መድቦ መንቀሳቀስ እና በዚህም ከልጆች ጋር ማሳለፍ ሊለመድ ይገባል፡፡

4. በልጆች የባህሪ ለውጥ አብዝቶ መጨነቅ አይገባም
ልጆችን መንከባከብ ለወላጆች ደስታን ይሰጣል፤ ሆኖም ልጆች ከህጻንነት ወደ ጉርምስና የሚሸጋገሩበትን የእድሜ ልዩነት በማየት የባህሪ ለውጡን ማስተናገድ ጥሩ ነው፡፡
ልጆች በየእድሜ እርከናቸው የተለያዩ የስሜት ለውጦች ማሳየታቸው ወላጆችን ሊያስጨነቅ ይችላል፡፡
ሆኖም ወላጆች የልጆቻቸውን እድሜ በማጥናት፥ ጭንቀታቸውን መቀነስ እና ከአንዱ የእድሜ ደረጃ ወደ ሌላኛው ሲሸጋገሩ የስሜት ወይም የባህሪ ለውጡ ሊመጣ ወይም ሊቀረፍ እንደሚችል ማሰብ ይኖርባቸዋል፡፡
ልጆች በአዲሱ የእድሜ እርከን ውስጥ ሲገቡም ያጋጠሟቸውን የባህሪ ለውጦች በመላመድ ሂደት ሊቀርፏቸው ይችላሉ፡፡
ወላጆችም ይህን ተረድተው ለልጆች የባህሪ አወንታዊ ለውጥ መፋጠን ከጭንቀት በራቀ መንፈስ ከጎን ሊቆሙ ግድ ነው፡፡

5. ወደ ራስ መመልከት (እኔ በባህሪየ ምን አይነት ሰው ነኝ ማለት)
ወላጅ የልጆች የነገ ማንነት መገንቢያ የመጀመሪያው መሰረት ወይም አርዓያ ነው፡፡
በመሆኑም ወላጆች አስተሳሰባቸውን፣ ተግባራቸውን፣ ባህሪያቸውን ወደ ራስ ዘወር አድርጎ መመልከት እና ለልጆች እንዴት አርዓያ ወይም በምን መልኩ ምሳሌ መሆን እንደሚገባ ማጥናት ተገቢ ነው፡፡
እናት እና አባት ሲቻል አለመጨቃጨቅ፥ ካልተቻለም የጭቅጭቁን ስፍራ ከልጆቻቸው ፊት ማራቅ ይኖርባቸዋል፡፡
ይህ ደግሞ ልጆች በቂ እንቅልፍ፣ መዝናናት እና ሌሎችም መልካም ነገሮችን እንዲያገኙ ይጠቅማቸዋል፡፡

6. እርዳታን መሻት
ወላጆች ለልጆቻቸው በደስታ ውሎ ማደር አብዝተው በሚጨነቁበት ጊዜ፥ ማድረግ ስላለባቸው ነገር ምክርን ወይም ሌሎች እርዳታዎችን መፈለግ እንዳለባቸው ተነግሯል፡፡
ልጆች ስለሚያስጨንቃቸው ወይም ስለሚያሳስባቸው ነገር በወላጆቻቸው ሲጠየቁ፥ ደስታን ሊሰጣቸው፣ ለውጥም ሊያመጣ ይችላል፡፡
ነገር ግን ስላጋጠማቸው ወይም ስላስጨነቃቸው ችግር ለወላጆቻቸው መናገር ላይፈልጉ ይችላሉ፡፡

ምንጭ:- ጤናችን