NEWS: በ2009 ከውጭ ሀገር ጎብኝዎች ከ3 ነጥብ 32 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ::

                                           

በጀት ዓመት ከውጭ ሀገር ጎብኝዎች ከ3 ነጥብ 32 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ።

በበጀት ዓመቱ 886 ሺህ 897 ጎብኝዎች ወደ ሀገሪቱ በመግባት የተለያዩ የቱሪዝም መስህቦችን መጎብኘታቸውንም ነው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያስታወቀው።

ባለፉት ስድስት ወራት የነበረው የቱሪስት ፍሰት በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ጭማሪ ማሳየቱም ተጠቅሷል።

በበጀት ዓመቱ በመጀመሪያው መንፈቀ አመት 439 ሺህ 359 ቱሪስቶች ሀገሪቱን የጎበኙ ሲሆን በዚሁ በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት ግን ቁጥሩ ከፍ ብሎ 447 ሺህ 538 ቱሪስቶች ሃገሪቱን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡ 

በሰላምና ፀጥታዋ በጎብኝዎች ዘንድ ተመራጭ የሆነችው ኢትዮጵያ ያሏት በርካታ የቱሪስት መስህቦች ጎብኝዎች በተደጋጋሚ እንዲያዘወትሯትና ተመራጭ አገር እንድትሆን አስችሏታል ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡

በበጀት ዓመቱ ሁለተኛ ሩብ ዓመት በሃገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋት በተወሰነ መጠን የቱሪስት ፍሰቱ ላይ የራሱ የሆነ ተፅእኖ አሳድሮ እንደነበር ያስታወሰው ሚኒስቴሩ፥ አሁን በተመለሰው ሰላምና መረጋጋት የቱሪስት ፍሰቱ ወደ ነበረበት ደረጃ እየተመለሰ መሆኑን አመላክቷል።

በ2009 በጀት አመት የተገኘው ገቢ ከ2008 ጋር ሲነፃጸር የ2 ነጥብ 5 በመቶ ቅናሽ ያሳየ ነው ተብሏል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement