NEWS: ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ግብር ከፋዮች ያመኑበትን ይከፍላሉ በሚል የተናፈሰው መረጃ ሀሰት ነው – አቶ ከበደ ጫኔ

                                                   

በበላይ ተስፋዬ

በቀን ገቢ ግምቱ ላይ ቅሬታ ያለው ማንኛውም የደረጃ ሐ ግብር ከፋይ አሳማኝ መረጃ ይዞ እስከመጣ ድረስ ተገቢ ምላሽ ይሰጠዋል አለ የኢትዮጵያ ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ጫኔ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ፥ በህጋዊ መንገድ ቅሬታን ማቅረብ እየተቻለ ሌላ ህገወጥ ድርጊት መፈፀም በህግ ያስጠይቃል ብለዋል።

በአዲስ አበባ 148 ሺህ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች የቀን ገቢ ግምት ተከናውኖላቸዋል።

በእለት ገቢ ግምቱ በገማቾች እና ነጋዴዎች መካከል የመረጃ ልውውጥ ችግር ነበር ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፥ በአብዛኛው የቀን ገቢ ግመታው ትክክል መሆኑን ገልፀዋል።

68 በመቶ የሚሆኑ የእለት ገቢያቸው የተገመተላቸው ሰዎች ትክክል መሆኑን አምነውበት ግብራቸውን መክፈል ጀምረዋል፤ 32 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ቅሬታ አቅርበዋል ብለዋል።

በአጠቃላይ 23 ሺህ ቅሬታዎች ቀርበው የ20ሺዎቹ የመጀመሪያው ግምት ፀድቆ መክፈል እንዳለባቸው ተወስኗል ነው ያሉት አቶ ከበደ።

በአጠቃላይ ከደረጃ “ሐ” የቀን ገቢ ግመታ ጋር ተያይዞ አሁንም የሚቀርቡ ቅሬታዎች ካሉ ባለስልጣኑ ለመፍታት ዝግጁ መሆኑንም አንስተዋል። 

የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች ግን የሂሳብ መዝገብ እና ካሽ ሪጂስተር ስላላቸው የእለት ገቢ ግምቱ አይመለከታቸውም ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ።

ዛሬ ማለዳ በአዲስ አበባ መርካቶ ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን እንዳይከፍቱ ቅስቀሳ ሲደረግ እንደነበርና የተወሰኑ ሱቆች እስከ እኩለ ቀን ድረስ ተዘግተው መቆየታቸውን ነው ያነሱት አቶ ከበደ።

ከአክሲዮን ማህበራት ጋር በተደረገ ውይይትም ነጋዴዎቹ በራሳቸው ተነሳሽነት ሳይሆን የቅስቀሳ ወረቀት እና የተለያዩ የስለት መሳሪያዎችን ይዘው የሚንቀሳቀሱ አካላት ዛቻ ምክንያት ሱቆቻቸውን ሊዘጉ መቻላቸውን አረጋግጠናል ብለዋል።

ከነጋዴዎቹ ማህበራት ጋር ከተደረገው ውይይት በኋላ መርካቶ በእኩለ ቀን ወደ መደበኛ እንቅስቃሴዋ መመለሷንም አንስተዋል። 

በስፍራው ነጋዴዎችን ሱቆቻቸውን እንዲዘጉ በሃይል ሲያስፈራሩ ከነበሩ ሶስት ግለሰቦች ውስጥም ሁለቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በዝቅተኛ የስራ ንግድ ላይ ግብር ከፋዮች ያመኑበትን ይክፈሉ ተብሏል በሚል ሲናፈስ የነበረው መረጃም ፍፁም ከእውነት የራቀ መሆኑንም ነው አቶ ከበደ ያነሱት።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

Advertisement