NEWS: በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑና ለልማት የሚነሱ ኤርትራውያን እንዴት ምትክ ቦታና ካሣ ይሰጣቸው የሚለው እስካሁን ውሣኔ አላገኘም ተባለ፡፡

                                         

(ትዕግስት ዘሪሁን)

ስለ ጉዳዩ ጥናት ተደርጎ ለመሬት ማኔጅመንት መቅረቡንም የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ ለሸገር ተናግሯል፡፡

ለሀገር ደህንነት ሥጋት አይደሉም የተባሉና ከኢትዮ-ኤርትራ ግጭት በፊት ሀብት ንብረት አፍርተው በአዲስ አበባ ይኖሩ የነበሩ ኤርትራውያን በከተማዋ ይኖራሉ፡፡

በመልሶ ማልማት ክልል ውስጥ ቤት ያላቸው ኤርትራውያን እንዴት ካሣና ምትክ ቦታ ማግኘት እንዳለባቸው ራሱን የቻለ ሕግ ስለሌለ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ ሲቸገር መቆየቱን ሰምተናል፡፡

ለጉዳዩ እልባት ለመስጠትም ከፍትህ ቢሮ ጋር ጥናት አካሂዶ ለመሬት ማኔጅመንት ማቅረቡን የኤጀንሲው ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ ግርማ ብርሃኑ ለሸገር ተናግረዋል፡፡

እስካሁን ግን ውሣኔ ያላገኘ ጉዳይ እንደሆነም ነግረውናል፡፡

ለመልሶ ማልማት ቤቶች ሲፈርሱ በየክፍለ ከተማው አንድም፣ ሁለትም የኤርትራውያን ጉዳይ ያጋጥመናል ያሉት አቶ ግርማ ከዚህ ቀደም ቤታቸው የፈረሰባቸው ምትክ ቦታና ካሣ አልተሰጣቸውም ብለዋል፡፡

ይሁንና የቤታቸውን ሁኔታና የቦታ ልኬታቸውን ሙሉ መረጃ ይዘናል በጥናቱ መሠረትም የከተማዋ ካቢኔ በሚያሣልፈው የውሣኔ ኃሣብ መሠረት ይስተናገዳሉ ብለዋል፡፡

አሁን ግን ለጊዜው ቤታቸው ያልፈረሰባቸው ኤርትራውያን አካባቢው ለመልሶ ማልማት ቢፈለግም ጉዳዩ ውሣኔ እስኪያገኝ ድረስ እንዳይፈርስባቸው ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡

ምንጭ:- የሸገር FM 102.1 ሬዲዮ

 

Advertisement