NEWS: በእህቱ ሞት ያዘኑትን እናቱን ለማስደሰት ለ20 ዓመታት ቀሚስ የለበሰው ቻይናዊ::

                                             

በቻይና ጉሊን ከተማ እህቱ ከሞተች ጀምሮ ለ20 ዓመታት የሴት ልብስ እየለበስ እናቱን የሚያፅናናው ጎልማሳ የብዙዎችን ልብ ነክቷል፡፡

በማህበራዊ ትስስር ድረ ገፆች የተለቀቀው የቪዲዮ ምስል እንደሚያሳየው ስሙ ያልተጠቀሰው ይህ ሰው የቼኦንሳም ባህላዊ ቀሚስ እየለበሰ ነው ከእናቱ ጋር ኑሮውን እየገፋ የሚገኘው፡፡

በአለባበሱ ብቻ ሳይሆን በፀጉር አሰራሩ ሁሉ ሴት እንጂ ወንድ አይመስልም፤ ሴት ልጃቸው ብትኖር ለእናታቸው የምታደርገውን ነገር እያደረገ ቀኑን ሙሉ እናቱን ይንከባከባል፡፡

ምንም ዓይነት ስራ እንደሌለው የተናገረው ይህ ጎልማሳ ዋሽንት እየነፋ ሰዎች በሚሰጡት ገቢ ነው እሱን እና እናቱን የሚያኖረው፡፡

ግለሰቡ የሴቶችን ቀሚስ እየለበሰ 20 ዓመታትን የዘለቀው ስለሚወደው ወይም ለሴቶች ልብስ ባለው ፍቅር ሳይሆን እናቱ የሴት ልጃቸውን ሞት እንዲረሱ እና ሀዘናቸውን እንዲያቆሙ ለማድረግ መሆኑን ተናግሯል፡፡

እናት ሴት ልጃቸው ከሞተች በኋላ የአዕምሮ መቃወስ ያጋጠማቸው ሲሆን፥ ወንዱ ልጃቸውም እናቱ ከዚህ ህመም እንዲድኑ እና ደስተኛ እንዲሆኑ በማሰብ ቀሚስ መልበስ ጀመረ፡፡

እናቱም ይህን የወንድ ልጃቸውን የሴት አለባበስ ስለወደዱለትና ደስተኛም ስለሆኑ ላለፉት 20 ዓመታት ያለማቋረጥ እየለበሰ ነው፡፡

ጎልማሳው “ለመጀመሪያ ጊዜ ቀሚስ ስለብስ እናቴ ደስተኛ ሆነች፤ እኔም የሴት ልብስ መልበሴን ቀጥልኩ፤ ላፉት 20 ዓመታትም እንደ ሴት እንጂ እንደ ወንድ ሆኜ አላውቅም” ነው ያለው፡፡

ሰዎች ወንድ ሆነህ ቀሚስ ለብሰህ ሲያዩህ ሊስቁብህ አሉታዊ ጫና ሊፈጥሩብህ አልሞከሩም ወይ ተብሎ ሲጠየቅ፥ “እኔ የእናቴ ደስታ እንጂ የሌሎች ሰዎች መጥፎ ንግግር ወይም ይስቁብኛል ብሎ መጨነቅ በአዕምሮየ ቦታ የለውም” የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡

እናቱም በልጃቸው ሞት ምክንያት በደረሰባቸውን ሀዘን ያጋጠማቸው የአዕምሮ መቃወስ እየተሸላቸው ሲሆን፥ ስለ ወንድ ልጃቸውም  “ሴት ልጄ ብትሞት ሌላ ሴት ልጅ ተተክታ እየተንከባከበችኝ ነው ድስተኛም ነኝ ” ብለዋል፡፡

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

Advertisement