የጥንዶቹ አስከሬን ከ75 አመታት በኋላ በበረዶ ግግር ላይ ተገኝቷል

                                  

በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት የት እንደገቡ ያልታወቁት ጥንዶች ከ75 አመታት በኋላ አስከሬናቸው ተገኝቷል።

ማርሴሊን እና ፍራንሲን ዱሞውሊን የተሰኙት ጥንዶች ስዊዘርላንዳውያን ሲሆኑ፥ በፈረንጆቹ ነሃሴ አጋማሽ 19 42 ከቤታቸው እንደወጡ አልተመለሱም።

ወዳጅ ዘመድና ልጆቻቸውም ለበርካታ ጊዜያት ፈልገው ስላጧቸው እርማቸውን አውጥተው ቁጭ ብለዋል።

ጥንዶቹ በወቅቱ ከዋና ከተማዋ በርን 201 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቻንዶሊን በተሰኘችው መንደር ይኖሩ ነበር።

የሰባት ልጆች ወላጅ የሆኑት ጥንዶቹ በወቅቱ የ40 እና 37 አመት እድሜ ሲኖራቸው፥ በግብርና ስራ ይተዳደሩም ነበር።

በተጠቀሰው ወቅትም የቤት እንስሳቱን ይዘው በአልፕስ ተራሮች በተከበበችው መንደር በሚገኘው ቫላይስ ወንዝን ተከትለው ለግጦሽ ይወጣሉ።

ይሁን እንጅ እንደወጡ አልተመለሱም በጊዜው ልጆቻቸውን ጨምሮ በርካቶች ፍለጋ ቢወጡም ሊያገኟቸው አልቻሉም ነበር።

ጥንዶቹ በትዳር ያፈሯቸው ህጻናት ልጆችም ከወላጆቻቸው የተለያዩ ቤተሰቦች ጋር ለመኖር ተነጣጥለው ኑሯቸውን ሲገፉ ቆይተዋል።

በወቅቱ የጠፉት ጥንዶች ግን ከ75 አመት በኋላ አስከሬናቸው አንድ ላይ ተገኝቷል።

                                                                                                      

አስከሬኑ በአካባቢው ባለ በረዷማ ስፍራ የውሃ አካል ላይ ተገኝቷል ነው የተባለው፥ ፖሊስም በወቅቱ ጥንዶቹ ያደረጉት ማጌጫና መሰል እቃዎች ባሉበት ተጣብቀው መገኘታቸውን ገልጿል።

በበረዶ ላይ የተገኘው የጥንዶቹ አስከሬንም በወቅቱ የጠፉት የዱሞውሊን ቤተሰቦች ስለመሆኑ አመላካች ሁኔታ ታይቷልም ነው ያለው ፖሊስ።

ጥንዶቹ በወቅቱ የቤት እንስሳቱን ለግጦሽ ባሰማሩበት ወቅት በበረዷማው ክፍል ላይ በሚገኝ ስንጥቅ ወደ ታች ወድቀው ሞተው ሊሆን ይችላል የሚል ግምቱንም አስቀምጧል ፖሊስ።

አሁን ላይም የዘረ ምል ምርመራ እየተደረገ ሲሆን፥ እስካሁን የታዩ ፍንጮች የጥንዶቹ አስከሬን የዱሞውሊን ቤተሰቦች መሆኑን እያመላከተ ነው።

በወቅቱ ወላጆቿ ሲጠፉ የአራት አመት ህጻን የነበረቸውና የአሁኗ አዛውንት ማርሴሊን ኡድሪ፥ በእለቱ እናታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ከአባታቸው ጋር እንስሳቱን ለግጦሽ ለማሰማራት መውጣታቸውን አስታውሰዋል።

በአብዛኛው አባታቸው እንስሳቱን ለግጦሽ የሚያሰማሩ ሲሆን፥ ይህም እናታቸው በተከታታይ በመውለዳቸውና አካባቢው ለነብሰ ጡር ሴት እንቅስቃሴ የማይመች ከመሆኑ ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የስዊዘርላንድ መንግስት በበኩሉ ከፈረንጆቹ 19 25 ጀምሮ በአልፕስ ተራሮች አካባቢ 280 ሰዎች መጥፋታቸውን አስታውሷል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ

 

 

Advertisement