የ40/60 ቤቶች ግንባታ በምህድስና ወይስ በፖለቲከኞች ውሳኔ?

የአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኃላፊዎች የሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ የሰማ ማንኛውም ሰው ሊያነሳ የሚችለው አንዱና ዋኛው ጥያቄ፣ እነዚህን ከፍተኛ የመንግስት ተቋማት የሚመሩ ኃላፊዎች የ40/60 የቤቶች ግንባታን የሚያከናውኑት በምህንድስና ሳይንስ ወይ በፖለቲካዊ መመሪያ ነው? ሚል ነው፡፡ ምክንያቱም በምህንድስና ሳይንስ ቢሆን ኖሮ፣ አንድ ሲደምር አንድ በአሜሪካን፣ በአውሮፓ፣ በኤዢያ፣ በላቲን አሜሪካ እንዲሁም በአዲስ አበባ ሁለት ነው መልሱ፡፡ በአዲስ አበባ መስተዳድር ውስጥ ግን አንድ ሲደመር አንድ በሚሰጠው ፖለቲካዊ ውሳኔ የሚወሰን እንጂ ሁለት መሆኑን ማንም ማረጋገጥ አይችልም፡፡

ለአብነት ያህል አንድ ሁለት ነጥቦች እናንሳ፡፡ ከ18 ወራት በፊት መቶ በመቶ ከቆጠቡ 11ሺ 88 ተወዳዳሪዎች መካከል፣ በሰንጋ ተራ እና በክራውን አካባቢ የተገነቡ የ40/60 የመኖሪያና የንግድ ቤቶችን በእጣ እንደሚያገኙ በአደባባይ ተገልፆ፤ በሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲተላለፉ ተደርጓል፡፡ የመጀመሪያው ምዝገባ ሲካሄድ፣ አንድ መኝታ ቤት 55 ካሬ ሜትር ሥፋት ያለው፤ ባለሁለት መኝታቤት 75 ካሬ ሜትር ሥፋት ያለው፣ ባለሶስት መኝታ ቤት ከ100 ካሬ ሜትር ሥፋት ያለው ነበር፡፡

ለ”ቆጣቢው” ሕብረተሰብ ሲተላለፍ፤  በምዝገባ ወቅት ባለአንድ መኝታ 55 ካሬ ሜትር የተባለው ታጥፎ፣ ወደ 124 ነጥብ 97 ካሬ ሜትር፣ ባለሁለት መኝታቤት ቀይሯል፡፡ በ75 ካሬ ሜትር ላይ ይገነባል የተባለው ባለሁለት መኝታ ቤት ታጥፎ፣ ወደ 149 ነጥብ 5 ካሬ ወደሆነ ሶስት ክፍል መኝታ ቤት ተቀይሯል፡፡ በ100 ካሬ ሜትር ታስቦ የነበረው ባለሶስት መኝታ ቤት ታጥፎ፣ ወደ 168 ነጥብ 68 ካሬ ሜትር ወደአለው ባለአራት መኝታ ቤት ተቀይሯል፡፡ የአንድ ካሬ ሜትር ክፍያም ከ3ሺ 200 ብር፣ ወደ 4ሺ 918 ብር አድጓል፡፡ በምህንድስና አዋቂዎች ተዘጋጅቷል የተባለው ንድፍ ተቀይሮ በሌላ ሲተካ፣ ውል የተሰጠው ቆጣቢው ሕብረተሰብ ፈቃዱ አልተጠየቀም፡፡ ለውጡን ተከትሎ በሚፈጠር ጭማሪ ገንዘብ የመክፈል አቅም ይኑረው፣ አይኑረው አልተጠየቀም፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝደነት አቶ በቃሉ ዘለቀ እንደገለጹት ከሆነ፤ “ለቆጣቢው ሕብረተሰብ በዕጣ ከቀረቡት 972 ቤቶች መካከል 324ቱ ባለሁለት መኝታ ቤቶች፣ 324ቱ ባለሶስት መኝታ እንዲሁም 324 ባለአራት መኝታዎች ናቸው፡፡” አቶ በቃሉ ሊመልሷቸው ከሚገቡና ምላሽ ካልሰጡባቸው ጥያቄዎች (ለሕዝቡ)፣ ባለአንድ መኝታ ሲታጠፍ እና ባለአራት መኝታ ቤት ሲገነባ ለቆጣቢው ሕብረተሰብ አሳውቃችኋል? ሕብረተሰቡ በውል ተነግሮት፣ ውል አስሮ ከጀመረው ቁጠባ አንፃር እንደባንክ ደንበኛ ከውል ውጪ ስትሰሩ ከሕግ አንፃር እንዴት ያዩታል? አዲስ ነው የተባለው የዲዛይን ለውጥ ሲደረግ ከሕብረተሰቡ ጋር መክራችሁበታል? የሚሉ ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

ከላይ የሰፈረውን የ”እንደልቡን ለውጥ” በገንዘብ ረገድ ያመጣውን ልዩነት እስኪ እንመልከተው፡፡ በምዝገባ ወቅት ባለሶስት መኝታ ቤት 386ሺ ብር፤ ባለሁለት መኝታ ቤት 240ሺ ብር በሙሉ ክፍያ የተፈጸመ ነው፡፡  እንዲሁም የአንድ ካሬ ሜትር ዋጋ በ3ሺ 200 ብር ስምምነት ሽያጭ የተፈጸመ ነበር፡፡ አዲስ በተደረገው ለውጥ ባለሁለት መኝታ ቤት ከ240ሺ ብር ወደ 614ሺ 602 ብር ከፍ ያለ ሲሆን፤ በተደረገው ለውጥ 347ሺ 602 ብር ጭማሪ አስከትሏል፡፡  ባለሶስት መኝታ ቤት ከ386ሺ ብር ወደ 829ሺ 568 ብር  ከፍ ያለ ሲሆን፤ በተደረገው ለውጥ 443ሺ 568 ብር ጭማሪ አስከትሏል፡፡ ይህንን ከፍተኛ መጠን ያለውን የገንዘብ ጭማሪ ከተጠቃሚው ሕብረተሰቡ ጋር ሳይመክሩበት ነው የተካሄደ ነው፡፡   

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ጌታቸው ኃ/ማሪያም በበኩላቸው፣ “የመጀመሪያው ዋጋ የተቀመጠው ለመነሻ እንዲሆን እንጂ ቤቱ ሳይሰራ ዋጋ አይቀመጥም” ብለዋል፡፡ አያይዘውም፣ “በምዝገባው ወቅት የተቀመጠው 3ሺ 200 ብር በካሬ ሜትር የማስተላለፊያ ዋጋ ለመመዝግብ እንደመነሻ እንዲሆን እንጂ ጭማሪ ሊኖር እንደሚችል የሚታወቅ መሆኑ ግልፅ ነው”፣ ባይ ናቸው፡፡ ሚኒስትሩ ይህን ምላሽ በሰጡበት የአንድ ካሬ ሜትር ዋጋ ከ3ሺ 200 ብር ወደ 4ሺ 918 ብር ከፍ እንዴት እንዳለ አላስረዱም፡፡

አቶ ጌታቸው ገለልተኛ የሚሏቸው ቡድኖች እነማን እንደሆኑ ባይታወቅም፣  “20 አባላት ባሉት ገለልተኛ የጥናት ቡድን አስተዳደሩ በግንባታ ያወጣው ወጪ ተመርምሮና ድጎማው ሁሉ ታስቦ የጥናቱ ውጤት ለመንግስት መቅረቡንና ውሳኔ መተላለፉንም” ተናግረዋል፡፡ “እንደጥናቱ ውጤት” ከሆነ አሉ አቶ ጌታቸው፣ “መጀመሪያውኑ 3ሺህ 200 ተብሎ የተቀመጠው የአንድ ካሬ ዋጋ በ4 ሺህ 120 ብር መቀመጥ እንደነበረበት የአጥኚዎቹ ቡድኖች አሳውቀውናል” ብለዋል፣ አቶ ጌታቸው ኃይለማርያም፡፡

የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው በበኩላቸው፣ የጋራ መከራከሪያ ነጥባቸውን ሲያጠናክሩ እንዳስቀመጡት፣ “በዕጣ የተላለፉት የ40/60 ቁጠባ ቤቶች የማስተላለፊያ ዋጋ በካሬ 4 ሺህ 918 ብር እንዲሆን መንግስት ውሳኔ አሳልፏል፡፡ እንዲሁም በጥናት ቡድኑ ውጤት መሠረት፣ የአንድ ካሬ ሜትር ማስተላለፊያ ዋጋ 5ሺህ 680 ብር ከ80 ሣንቲም ነበር፡፡ ይሁንና አስተዳደሩ ከእያንዳንዱ ካሬ ሜትር ላይ 762 ብር በመቀነስ ወይም ድጎማ በማድረግ፣ በካሬ 4 ሺህ 918 ብር እንዲሆን የመወሰኑ “አዛኝነታቸውን” ከፍ አድርገው ለቆጣቢው ሕብረተሰብ የብሥራት ዜና ተናግረዋል፡፡

አቶ አባተ አያይዘውም እንዳሉት፣ “ከጥናቱ ዋጋ ቅናሽ ያደረገውም፣ አስተዳደሩ ለዜጎቹ የገባውን ቃል  ለማክበር እና ዜጎቹ ላይ ጫና ላለማሳደር ስለሚፈልግ እንዲሁም፣ ቤቶቹ ከተባለው ጊዜ በመዘግየታቸውና የመጀመሪያዎቹ ባለዕጣዎች በመሆናቸው ነው፤” ሲሉ ለሕዝብ ያላቸውን ተቆርቋሪነት ሊያንጸባርቁ ሞክረዋል፡፡

የአዲስ አበባ የቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይሉ ቀነአ የዋጋ ጭማሪ እንዴት እንደተፈጠረ ሲያብራሩ፣ “የንድፍ ለውጥ ሲመጣ የተከተለው የቤቶች ስፋት መጨመር እንዲሁም ከፒቪሲ መስኮት ወደ አልሙኒየም፣ ከኤጋሺት የጣሪያ ክዳን ወደ ሲሚንቶና ጠጠር ውህደት ክዳን መለወጥ እና የመዋቅራዊ ንድፍ ለውጥ መደረጉም የዋጋ ጭማሪ እንዳስከተለ” አስቀምጠዋል፡፡ ሆኖም አቶ ኃይሉ፣ ዋጋ ለማስተካከል ኔጌቲቪ ቦታዎችን ወደ ፓዘቲቭ ቦታዎች በመቀየር ተጠቃሚው ላይ ጫና ማድረስ አለማድረሳቸውን በግልፅ አላስቀመጡም፡፡

አያይዘውም፣ “ባለሁለት መኝታ ቀድሞ የተያዘለት ስፋት 75 ካሬ ሜትር ነበር፡፡ አሁን ለባለአንድ የታሰበው ነው ወደ ባለሁለት መኝታነት ከፍ ብሎ የመጣው፡፡ ያም ሆኖ 124 ካሬ ሆኗል፡፡ 75 ካሬው ቀድሞ በተቀመጠለት መነሻ ዋጋ (3ሺህ 200 ብር) ሲሰላ፣ መቶ በመቶ ቆጥበው ለዛሬው ውድድር የተዘጋጁት ተመዝጋቢዎች እያንዳንዳቸው 240 ሺህ ብር ከፍለዋል፡፡ በዚህ ዋጋ ቤታቸውን ለመረከብም የተዘጋጁ ነበሩ፡፡” ይሁንና አሉ አቶ ኃይሉ፤ “ባለ ሁለት መኝታው አሁን ከፍ ብሎ 124 ነጥብ 97 ካሬ ደርሷል፡፡ በአዲሱ የማስተላለፊያ ዋጋ 4 ሺህ 918 ብር ስናሰላው የቤቱ ዋጋ ወደ 614 ሺህ 602 ብር ከ46 ሳንቲም ያሻቅባል፡፡ ይህም የቤት ዕድለኞቹ ቤቱን ለማግኘት ቀድመው ከከፈሉት ተጨማሪ 374 ሺህ 602 ሳንቲም ይጠየቃሉ በማለት፤” የአቶ አባተ ስጦታውን፣ የአዛኝ ቂቤ አንጓች ምላሽ አፈር በአፈር አድርገውታል፡፡

ለሕብረተሰቡ ከተገባው የውል ክፍያና የማስተላለፊያ ወጪ ልዩነት አንፃር፣ ሕብረተሰቡን ሳያናግሩ በተለይ ከመቶ ፐርሰንት በላይ ጭማሪ ማድረግ፣ በአሰራር የተለመደ አይደለም፡፡ በኮንስትራክሽን ሥራዎች፣ ደንበኛውን ሳይጠሩ ከሁለት በመቶ እስከ አምስት በመቶ ክለሳ ማድረግ የተለመደ አሰራር ነው፡፡ እነ “እንደልቡ” ግን በሰጡት መግለጫ ላይ፣ “ቀድሞ በውሉና መመሪያው ላይ የዋጋ ጭማሪ ምክንያታዊ በሆነ አግባብ ሊኖር እንደሚችል መቀመጡን” ለመከራከሪያ ነጥባቸው ማፅኛ አድርገው አቅርበዋል፡፡

 እነዚህ ኃላፊዎች ጨምረውም፣ “በባለአራት መኝታዎች ላይ፣ ዋጋ ከብዶኛል የሚሉ ካሉ አስተዳደሩ በሁለተኛው እና በሌላ ዙር ደግመው በእጣ እንዲካፈሉ እንደሚያደርግ ገልፀው፣ ባለአራት መኝታዎቹን የሚፈልጓቸው ተመዝጋቢዎች ካሉ ቅድሚያ ለመስጠት በሚል እንጂ መጀመሪያውኑም ተመዝጋቢ ስለሌለባቸው መስተዳድሩ መረከብ ይችል እንደ ነበር አስረድተዋል፡፡ እንዲሁም፣ “ቅድሚያ ለቤት ፈላጊ ዜጎች በሚል ቅን ሃሳብ መነሻ መሆኑን” አንስተው አዛኝነታቸውን ለሕብረተሰቡ ሊያቋድሱ ሞክረው ነበር፡፡ የሚገርመው በሕብረተሰቡ ገንዘብ በውል ያልሰፈረ ቤት መገንባታቸው ሳያሳፍራቸው፣ ባለአራት መኝታ ቤት የዕጣ ውድድር ላይ እንዲሳተፉ የተደረጉት ቅድሚያ ለቤት ፈላጊ ዜጎች በሚል “ቅን ሃሳብ” ነው እያሉ፣ ሕብረተሰቡ በቆጠበው ገንዘብ እና ሞራል ላይ የሚያላግጡ፣ የማይመጥኑትን ኅብረተሰብ የሚመሩ መስተዳድርና የገንዘብ ተቋማት ማየት እንዴት እንደሚያሳዝን ማን በነገራቸው?

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ዋለልኝ ለመንግሰት ሠራተኞች ቅድሚያ መሰጠቱን ከፍ ባለ ድምጽ እንዲህ ነበር ያሉት፣ “በዛሬው 972 ቤቶች እጣ ላይ 20 በመቶ የመንግስት ሠራተኞች ቅድሚያ የሚሰጣቸው ይሆናል፡፡ ….አስተዳደሩ በእነዚህ ቤቶች ላይ ከ725 ሚሊዮን ብር በላይ ደጉሟል፤” ነበር ያሉት፡፡ አንደኛ፣ ቁጠባ ከጀመረው ሕብረተሰብ ከተወጣጡ ወገኖች የተሳተፉበት ጥናት ሳይቀርብ፣ በቃሉ የማይገኝ አስተዳደር 725 ሚሊዮን ብር ድጎማ አድርጊያለሁ፤ ማንም አይቀበለውም፡፡ ስለመደረጉም ምንም ማረጋገጫ የለውም፡፡ የመንግስት ሠራተኛውን በተመለከተ አቶ ዋለልኝ ሊመልሱት የሚገባው፣ የትኛው ሠራተኛ ነው፣ መቶ በመቶ የከፈለውን ክፍያ ከመቶ እጥፍ በላይ ተጨማሪ ዋጋ ተጠይቆ፣ አቀረብንልህ የምትሉትን ሃያ በመቶ የእጣ ውድድር እድል ተከፍቶልኋል ሲባል፣ በደስታ እና በፍቅር የሚቀበለው? ወይ የመንግስት ሠራተኛ ከሚሰራበት መስሪያቤት ጋር በተያያዘ ገቢው ይለያይ ይሆን?

የሥራ ኃላፊዎቹ አሰራራችሁ፣ የ40/60 ቤቶች ግንባታ ላይ የተሳተፈውን ሕብረተሰብ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው ተብለው ቢጠየቁም፣ አይናቸውን በጨው አጥበው፣ “ከ164 ሺህ ገደማዎቹ ተመዝጋቢዎች መካከል፣ 140 ሺህዎቹ ቁጠባቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን አውስተው፤” ምላሽ የሰጡት፡፡ የተንጠባጠቡት 24ሺ ዜጎች ግን ለእነሱ ምናቸውም አይደሉም፡፡ በቀጣይ ደግሞ አሁን ከፈጸሙት ምክንያታዊ ያልሆነ፣ አሰራር እና ጭማሪ ሳቢያ ምን ያህሉ ከዚህ የ40/60 የቤቶች ግንባታ ፕሮግራም ውጪ ራሱን እንደሚያደርግ በጊዜ ሂደት የሚታይ ነው፡፡

እነዚህ የ”አደባባይ ጉዶች” እንዲህም ሲሉ ራሳቸውን በአደባባይ ወንጅለዋል፣ “ባለ አራት መኝታ ቤቶች ያለእቅድ መምጣታቸውን መነሻ በማድረግ፣ የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ (የአሁኑ የቤቶች ኮርፖሬሽን) ቤቶቹ እንዲሰጡት ጠይቆ እንደነበር” በምክትል ከንቲባው በአቶ አባተ ስጦታው በኩል ያለሃፍረት ተናግረዋል፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፣ “ባለ አራት መኝታ ቤቶች ያለ እቅድ መምጣታቸውን”  ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው፤ በቁጠባ ፕሮግራም የታቀፈው ሕብረተሰብ ከመሠረታዊ ፍጆታዎቹ ሳይቀር ሳስቶ  ሳያምርበት ሳያጌጥ ያስቀመጠው ገንዘብ በአዲስ አበባ አስተዳደር “ያለዕቅድ የቆጠበው ገንዘብ ይረጭበታል”፡፡ ለምን እንኳን ቢልም፣ መክፈል ካቻልክ በቀጣይ ዙር ጠብቅ፤ አቅም ያላቸው ይወስዱታል፤ እያሉ ያላግጡበታል፤ በገዛ ገንዘቡ፡፡ ወዴትስ አቤት ይላል፤ በሕግ የበላይነት የማይዳኙ የዛሬ ጊዜ ባለሟሎች ሁሉም በእጃቸው ሆኖ እየተሰማቸው ነው፡፡ ትልልቹም ደከማቸው፤ ለግምገማ ቢያስቀምጧቸው በዘረጉት የኔትዎርክ መረብ ተመልሰው ኃላፊ ሆነው ብቅ ይሉባቸዋል፡፡ እንዳይታገሏቸው የኔትዎርኩን መረብ ያጋፍጧቸዋል፡፡ ቀጣዩ ጥያቄ ማን ይታገላቸው? የሚለው ብቻ ነው፡፡       

በርግጥ እውነታቸውን ከሆነ፣ አንድ ጥሩ ነገር ተናግረዋል፣ ከሕጋዊ እጣ አወጣጥ ሥነሥርዓት ውጪ “ለባለስልጣኖች አንድም ቤት ለማንም አልተሰጠም” ሲሉ ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል፡፡ አቶ በቃሉ በበኩላቸው፣ “972ቱንም ቤቶች ቆጥረው እንደተረከቡና በምንም አይነት ውሳኔ አንድም ቤት ለማንም እንዳልተሰጠ” አረጋግጠዋል፡፡

ንግሥት በ2009 ዓ.ም. በጀት፣ 18ሺ 496 ቤቶችን ሰርቶ ለተጠቃሚዎች እንደሚያስተላልፍ ያሳወቀ ቢሆንም፣ ከፈላጊው ብዛት አኳያ ጠብ ያለ ነገር እስካሁን የለም፡፡ አጥጋቢም ባይሆን፣ ሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም.  የአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ የገነባቸውን የ40/60 ቤቶች  በይፋ ለ”እድለኞች” አስተላልፏል፡፡ የተላለፉት ቤቶች ጠቅላላ ብዛት 1 ሺ 292 ሲሆኑ፣  ከእነዚህ ውስጥ 972 የመኖሪያ ቤቶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ የንግድ ቤቶች ናቸው ተብሏል፡፡

ምንጭ፡ሰንደቅ ጋዜጣ

Advertisement