የሃዋይ ፍርድ ቤት በትራምፕ የጉዞ ክልከላ ላይ ማሻሻያ አደረገ

 የአሜሪካ ሃዋይ ግዛት ፍርድ ቤት በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጉዞ ክልከላ ላይ ማሻሻያ አደረገ።

ፍርድ ቤቱ ከዚህ ቀደም በፕሬዚዳንት ትራምፕ በተጣለው የጉዞ ክልከላ አዋጅ ላይ፥ የቅርብ ዝምድና ለሚለው ሰፋ ያለ ትርጉም በመስጠት ነው ማሻሻያውን ያደረገው።

በትራምፕ የክልከላ አዋጅ መሰረት የቅርብ ዝምድና የሚለው፥ አያትን ጨምሮ አክስት፣ አጎት፣ የአክስት ወይም የአጎት ልጅ፣ ምራትና አማችን አያካትትም ነበር።

የፍርድ ቤቱ ዳኛ ዴሪክ ዋትሰን፥ በአዲሱ ማሻሻያ መሰረት እነዚህ የቅርብ ዝምድናዎች በክልከላ አዋጁ ሊካተቱ አይገባም ብለዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ በጉዞ ክልከላው የቅርብ ዝምድና የሚለውን ሃረግ ጠባብ በሆነ መልኩ ታይቶ ነበር።

“የቅርብ ዝምድና “ ለሚለው ሃረግ የተሰጠው ትርጉምም ውስንና ጠባብ ነው በማለት ውሳኔውን ኮንነውታል።

ይህን ተከትሎም ክልከላው በዚህ መልኩ ሊተገበር አይገባም በማለት የተጠቀሱት ዝምድናዎች ከክልከላው ውጭ ይሁኑ በማለት ትዕዛዝ አሳልፈዋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት መተግበር የጀመረው የጉዞ ክልከላ እና አዲሱ የጉዞ ሰነድ አሰጣጥ፥ ከሊቢያ፣ ሶሪያ፣ ኢራን፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን እና የመን ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ይከለክላል።

የትራምፕ ፕሬዚዳንታዊ ውሳኔ በእነዚህ ሃገራት ዜጎች ላይ የ90 ቀናት የጉዞ ክልከላ እንዲሁም በስደተኞች ላይ የ120 ቀናት ክልከላ እንዲጣል ያዛል።

መመሪያው መተግበር ከጀመረበት እለት አንስቶም ለ90 ቀናት በአሜሪካ ህጋዊ የኑሮ ፈቃድ ያለው ቤተሰብ፣ እጮኛ፣ ልጅ ወይም ሌላ የቅርብ ዘመድ የሌለው ሰው ወደ አሜሪካ መግባት እንደማይችል ይደነግጋል።

በአዲሱ የሃዋይ ፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረት ደግሞ የቅርብ ዝምድና የሚለው ሰፋ ባለ መልኩ ይታያል።

በዚህ መሰረት አያት፣ አክስት፣ አጎት፣ የአክስት ወይም የአጎት ልጅ፣ ምራትና አማች በጉዞ ክልከላው እንዳይካተቱ ያዛል።

የአሜሪካ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፊታችን ጥቅምት ወር ፕሬዚዳንቱ ስደተኞች ወደ ሀገሪቱ እንዳይገቡ ያወጡት የጉዞ ክልክላ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ይሁን አይሁን የሚለውን ጉዳይ እንደሚመለከተው ይጠበቃል።

ምንጭ፡-FBC

 

Advertisement