አብጃታ ሻላ ሶዳ አሽ ፋብሪካ የአብጃታ ሃይቅን ህልውና እየተፈታተነ ነው-የሃይቁ 50 በመቶ የውሃ መጠን ደርቋል

የአብጃታ ሻላ ሶዳ አሽ ፋብሪካ  በበኩሉ ሃይቁ እየደረቀ ያለው በፋብሪካው ሳቢያ ሳይሆን በሌሎች ተደራራቢ ችግሮች ምክንያት ነው ብሏል።

አብጃታ ሃይቅ ባለፉት ሰባት አመታት ውስጥ 67 ስኩየር ኪሎ ሜትር  ውሃ መቀነሱን  የሃይቁ  ጥናትና ምርምር ባለሙያ  አቶ ተክለብርሃን ኪዳኔ ተናግረዋል።

የሃይቁ ስፋት በ1999 ዓ.ም ከነበረበት 163 ስኩየር ኪሎ ሜትር  በ2006 ዓ.ም በተደረገ ጥናት ወደ 96 ስኩየር ኪሎ ሜትር ዝቅ ብሏል።

የአብጃታ ሻላ ሃይቆች ብሄራዊ ፓርክ የቱሪዝምና የህብረተሰብ ዋርድ አስተባባሪ  አቶ ሜኤሶ ሃምዲኖ እንዳሉት  የአብጃታ ሻላ ሶዳ አሽ ፋብሪካ ውሃ አጠቃቀም የሃይቁን ህልውና እየተፈታተነው ነው።

በአሁኑ ሰዓት የሃይቁ  ውሃ መጠን ከ50 በመቶ በላይ መቀነሱንና  ካሁን በፊት ይሰጥ የነበረው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በከፍተኛ ሁኔታ  እየቀነሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

እንደ  አቶ ሜኤሶ ገለጻ “አብጃታ ሃይቅ ከዚህ በፊት ከፍተኛ የአሳ ሃብት እርባታ የሚካሄድበትና  የቱሪስት ፍሰት ያስተናግድ ነበር።”

ይሁን እንጂ  በአሁኑ ወቅት ሶዳ አሽ  የሚያመርተው ይህ ፋብሪካ የሃይቁን  ውሃ በብቸኝነት እየተጠቀመ ስለሚገኝ ሃይቁ በከፍተኛ ሁኔታ በመድረቅ ላይ ይገኛል ብለዋል።

ሶዳ አሽ ፋብሪካው የአብጃታ ሃይቅን ካደረቀና ከአገልግሎት ውጭ ካደረገ በኋላ ፕሮጀክታቸውን  በሌላኛው የሻላ ሃይቅ  ለመጀመር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሃይቁን ሃላፊዎችና የአካባቢውን ነዋሪ ስጋት ላይ ጥሏል ነው ያሉት አቶ መኤሶ።

በአሁኑ ጊዜ ወደ ሃይቁ ለጥናትና ምርምር እንዲሁም ለጉብኝት የሚመጡ ጎብኚዎች ቁጥር እያሽቆለቆለ እንደሚገኝም አክለዋል።

ሃይቁ በአሁኑ ሰኣት ቀድሞ ከነበረው አስራ አራት ሜትር ጥልቀት ወደ ሶስት ሜትር መቀነሱን የአብጃታ ሃይቅ  ጥናትና ምርምር ባለሙያው አቶ ተክለብርሃን ኪዳኔ ጠቁመዋል።

የሶዳ አሽ ፋብሪካ የአብጃታ ሃይቅ ውሃን ከበቂ በላይ በመጠቀሙም የአሳ ዝርያዎች ሙሉ ለሙሉ የጠፉ ሲሆን የባህር  አዕዋፋት ዝርያዎችም በከፍተኛ ሁኔታ በመመናመን ላይ እንደሚገኙ አቶ ተክለብርሃን ገልጸዋል።

ጉዳዩ የአየር ንብረት ለውጥን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያዛባና የተፈጥሮ መስህቦቻችንን የሚቀንስ በመሆኑ መንግስት አስቸኳይ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ አቶ ተክለብርሃን ጠይቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ሃይቁ በመድረቁ ምክንያት ሰባት ኪሎ ሜትር ያክል ስፋት ወደ ውስጥ መቀሱን ነው ተመራማሪው ጨምረው የተናገሩት።

 

ሃይቁ በአሁኑ ወቅት የያዘው የውሃ መጠን ለፋብሪካዉ በቂ ባለመሆኑ ምክንያት ወደ ሻላ ሃይቅ ለማዘዋወር ፋብሪካው እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ተመራማሪው ጠቅሰዋል።

ሻላ ሃይቅ የአብጃታ እጣ ፈንታ እንዳይገጥመው  ስጋት ገብቶናል ሲሉ አቶ ተክለብርሃን ተናግረዋል።

የአብጃታ ሻላ ሶዳ አሽ ፋብሪካ ስራ እስኪያጅ ዶክተር ብርሃነ መስቀል አመዴ  በበኩላቸው ፋብሪካው የሶዳአሽ ምርት ለማምረት ውሃ የሚጠቀመው ከሃይቁ  ቢሆንም ለመድረቁ ዋናው መክንያት ግን ይሄ አለመሆኑን ይናገራሉ።

እንደ ስራ አስኪያጁ ገለጻ የሃይቁ ህልውና የተመሰረተው በሌሎች ገባር ወንዞች ላይ በመሆኑ  በአሁኑ ሰዓት በአካባቢው በተፈጠረው ኢንቨስትመንትና ገባር ወንዞቹ ለመስኖ ስራዎች አገልግሎት እንዲውሉ በመደረጉ ምክንያት ወደ ሃይቁ ስለማይገቡ ሃይቁ መቀነሱን ይናገራሉ።

በተጨማሪም  በአለም ላይ በተፈጠረው ሙቀት ሳቢያ የሃይቁ ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ ትነቱ አየጨመረ ስለመጣ ለሃይቁ መቀነስ ሌላው መክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

ፋብሪካውን ከአብጃታ ወደ ሻላ ሃይቅ ለማዘዋወር እየተሰራ  ቢሆንም  ሻላ ሃይቅ ጥልቅና ምንጭ ያለው በመሆኑ በፋብሪካው ምክንያት የአብጃታ ሃይቅ እጣ ፈንታ እንደማይገጥመው ተናግረዋል።

በሻላ ሃይቅ ላይም ፋብሪካው የአዋጭነትና የአካባቢ ደህንነት ጥናት በባለሙያዎች እያስጠና እንደሚገኝ አክለው ገልጸዋል።

ምንጭ-ኢዜአ

 

Advertisement