የቀድሞው የፊፋ ስራ አስፈጻሚ አባል ብሌዘር ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (ፊፋ) ስራ አስፈጻሚነትን ጨምሮ በሌሎች የሃላፊነት ቦታ ላይ የሰሩት ቼክ ብሌዘር በ72 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

ከካንሰር ህመማቸው ጋር ሲታገሉ የቆዩት ብሌዘር፥ በተወለዱ በ72 ዓመታቸው ከዘህ ዓለም መለየታቸውን ጠበቃቸው አስታውቋል።

ከ1997 እስከ 2013 ድረስ የፊፋ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል በመሆን ያገለገሉት ብሌዘር፥ ከ1990 እስከ 2011 የሰሜንና መካከለኛው አሜሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ጸሀፊ እንዲሁም የአሜሪካ እግር ካስ ፌዴሬሽን ምክትል ስራ አስፈጻሚ በመሆን አገልግለዋል።

ብሌዘር ከፊፋ በተጨማሪም የሰሜንና መካከለኛው አሜሪካ እግር ኳስን በበላይነት መምራታቸው ይታወሳል።

ግለሰቡ ከሙስና ጋር በተያያዘ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2015 ጀምሮ ከማንኛውም እግር ኳሳዊ እንቅስቃሴ መታገዳቸው ይታወሳል።

በህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ ሙስና እና ከግብር ስወራ ጋር በተያያዘ ተሳትፎ አድርገዋል በሚል ነበር እድሜ ልክ ከእግር ኳሳዊ እንቅስቃሴ የታገዱት።

ብሌዘር የቀድሞው የፊፋ ፕሬዚዳንት ዮሴፍ ሴብ ብላተር ከሃላፊነታቸው እንዲነሱም አስተዋጽኦ እንደነበራቸው ይነገራል።

በግለሰቡ ዙሪያ አስተያየት የሚሰጡ ደግሞ በእግር ኳስ የተወዛገበ ታሪክ እንዳላቸው ይናገራሉ።

ምንጭ፦ FBC

 

Advertisement