ኢትዮቴሌኮምን ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ አሳጥተዋል የተባሉ ግለሰቦች ተፈረደባቸው

ኢትዮ ቴሌኮምን ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ አሳጥተዋል የተባሉ ሁለት ግለሰቦች በፅኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጥተዋል፡፡

ህጋዊ የቴሌኮም አገልግሎት የመስጠት ፍቃድ ሳኖራችው የተለያዩ የቴሌኮም አገልግሎት መስጫ መሳሪያዎችን በመጠቀም ኢትዮ ቴሌኮምን ከሶስት ነጥብ ሰባት ሚሊየን ብር በላይ ያገኝ የነበረውን ገቢ አሳጥተዋል የተባሉ ሁለት ተከሳሾች ናቸው በፅኑ እስራትና በገንዘብ የተቀጡት፡፡

የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት የቅጣት ውሳኔ ያስተላለፈባቸው ያልኑር መሀመድ እና አብዱሰላም ኑር በተባሉ ግለሰቦች ላይ ነው፡፡

ግለሰቦቹ በድሬደዋ ከተማ ቀበሌ 06 ልዩ ቦታው ኒያላ ሆቴል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በነበራቸው አንድ ሆቴልና መኖሪያ ቤት የተለያዩ ለቴሌኮም አገልግሎት የሚውሉ መሳሪያዎችን በመጠቀም ኢትዮ ቴሌኮም የዘረጋውን ኔትዎርክ በመቆጣጠር ወደ ተለያዩ ሀገራት ስልክ በማስደወልና እንዲደወል በማድረግ ወንጀል መፈጸማቸውን ነው የክስ መዝገባቸው የሚያስረዳው፡፡

ግለሰቦቹ ከህዳር 14 ቀን 2006 ጀምሮ እስከ ግንቦት 19 ቀን 2006 ዓመተ ምህረት ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ 206 ሀገራት የስልክ ጥሪዎችን በማድረግ ከአንድ ሚሊዮን ደቂቃዎች በላይ ጥሪዎችን አስተላልፈዋል፡፡

እነዚህ የስልክ ጥሪዎች ኢትዮ ቴሌኮም በዘረጋው ኔት ወርክ ቢያልፉ ኖሮ ድርጅቱ 3 ሚሊዮን 790 ሺህ380 ብር ያገኝ እንደነበርም ዓቃቤ ህግ ያቀረበው የክስ ቻርጅ ያሳያል፡፡

ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎትም የቀረበለትን የሰው፣የሰነድና የኤግዚቢት መረጃዎችን በመመርመርና የተለያዩ የቅጣት ማቅለያዎችን በማካተት አንደኛ ተከሳሽ ያልኑር መሀመድን በ10 ኣመት ፅኑ አስራትና በ90 ሺህ ብር ሁለተኛ ተከሳሽ አብዱሰላም ኑርን ደግሞ በስምንት ዓመት ጽኑ እስራትና በሀምሳ ሺህ ብር እንዲቀጡ ወስኗል፡፡

ምንጭ፡ኢዜአ

 

 

 

Advertisement