አዲስ አበባ ለ2010 በጀት ዓመት ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ ተበጀተላት

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ለ2010 በጀት ዓመት ከ40 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አጸደቀ።

 ምክር ቤቱ ለቀጣዩ ዓመት 40 ቢሊዮን 500 ሚሊዮን 282 ሺ 660 ብር  በጀት አጽድቋል።

 በጀቱ ከታክስ ነክ፣ ታክስ ካልሆኑ እና ከማዘጋጃ ቤት ገቢዎች፣ ከመንገድ ፈንድ እንዲሁም ከውጭ እርዳታና ብድር የሚገኝ ነው።

 የጸደቀው በጀት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ14 ነጥብ 4 በመቶ ወይም 5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ብልጫ ዓለው።

 በጀቱ የተመደበው በከተማይቱ ለሚከናወኑ የመንገድ ፣የመጠጥ ውሃ ፣የጤና ፣ የትምህርት ፣ የትራንስፖርት ፣ የፀጥታና ፍትህ ፣ የአረንጓዴ ፣ የፅዳትና ፓርክ ልማት ስራዎችን ለማከናወን ይውላል።

 የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት፣ መሬት ልማትና ማኔጅመንት፣ ቤቶች ልማት እና ሌሎችም በጀቱ የተመደበላቸው ዘርፎች እንደሆኑም ታውቋል።

ድህነትን በመቀነስና እድገትን በማፋጠን ወሳኝ ሚና ለሚጫወቱ የልማት መስኮች፣ ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ የካፒታል ክምችት ለሚያሳድጉና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን የሚያረጋግጡ ዘርፎችም የበጀት ዓመቱ የትኩረት መስኮች ናቸው፡፡

 ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት በመስጠት የዜጎችን እርካታ ለማረጋገጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት፣ በአንደኛና ሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውጤታማ አፈጻጸሞችን ይበልጥ ለማሻሻል፣ የዘላቂ ልማት ግቦችን ታሳቢ በማድረግ ነው በጀቱ የተዘጋጀው።

 የከተማው ምክር ቤት አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሶስተኛ መደበኛ ጉባኤ እስከ ፊታችን ሐሙስ ድረስ የሚቆይ ይሆናል።

ምንጭ፡ኢዜአ

 

Advertisement