“ቺርስ”- ለኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች ወዳጅነት (አፈንዲ ሙተቂ)

 ወትር ስለኤርትራ በምጽፍበት ጊዜ የሚሰጠኝ አስተያየት (Comment) ከወትሮው ይበዛል፡፡ እነኝህ ኮሜንቶች በዓይነታቸውም ይለያያሉ፡፡ በአድናቆት ከሚያንቆለጳሱኝና የሌለኝን ብቃት እየተረኩልኝ የሰማይ ጥግ ሊያደርሱኝ ከሚሞክሩት ጀምሮ “ህልመኛ ነህ፤ በቁምህ አትቃዥ፣ ኤርትራዊያን ደመኛ ጠላቶቻችን ናቸው” እስከሚሉት ድረስ ዓይነተ-ብዙ ናቸው፡፡ “የሻዕቢያ ስውር አርበኛ፣ የወያኔ ተላላኪ፣ የህዝቡን ትኩረት ከወያኔ ወደ ኤርትራ ለመውሰድ የሚጥር ድብቅ ሸረኛ፣ የታላቋ ኢትዮጵያ ህልም ተንበርካኪ፤ የጋሽ መንግሥቱ ትውልድ አባል” የማይባል ነገር የለም፡፡ በፌስቡክ ቆይታዬ ሁሉንም የለመድኩት በመሆኑ በሆዴ “እሰይ! አበጀሁ” እያልኩ ዝም ብዬ እነጉዳለሁ፡፡

አሁንም ግን እደግመዋለሁ!! እኔ ህልመኛ ነኝ! ይህ የኔ ህልም በፈጣሪም ሆነ በሰው ልጆች ዘንድ “ብሩክ” ተብሎ የሚወደስ ነው፡፡ ስለህዝቦች ፍቅር፣ ህብረት፣ አንድነትና እኩልነት ማለም የዘወትር ተግባሬ ነው፡፡ መቼም ቢሆን ይህንን ከማቆም ወደ ኋላ አልልም፡፡ እንኳንስ በደንብ የማውቃቸውን የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝቦችን ይቅርና አምስቱ የምስራቅ አፍሪቃ ሀገራት (ሱዳን፣ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲና ኤርትራ) በኮሎኒያሊስቶች የተሰመሩ ድንበሮችን በጣጥሰው በአንድ ግዛት ስር እንዲጠቃለሉ በጽኑ አልማለሁ፡፡ ምን ይሄ ብቻ! ትልቋ እማማ አፍሪቃም አንድ ሀገር እንድትሆን በብርቱ ነው የማልመው፡፡
*****
ኤርትራና ኢትዮጵያ ሰው ሰራሽ ችግሮች በቆሰቆሷቸው አቧራዎች መነሾነት ሁለት ሀገር ሆነዋል፡፡ ፍቺያችን በደም የታጀበ መሆኑ በጣም ያሳዝነናል፡፡ ያስለቅሰናል፡፡ ይህ ማለት ግን “አንድ ላይ የመሆናችን ጉዳይ ለዘልዓለሙ አብቅቶለታል” ማለት አይደለም፡፡ ሰው ሰራሽ ድንበር በኛ መካከል ቢሰመርም ባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋና ጂኦግራፊ በአንድ ላይ ያስተሳስረናል፡፡ የህዝቦቻችን የጋራ ታሪካዊ ውቅር መቼም ቢሆን አይፋቅም፡፡

እኛና ኤርትራዊያን በጣም ነው የምንመሳሰለው፡፡ እንዲህ የሚመሳሰሉ ህዝቦች የማታ ማታ ተመልሰው አንድ የሚሆኑበትን ሁኔታ የዓለም ታሪክ አሳይቶናል፡፡ ሁለቱ ጀርመኖች ከአርባ አምስት ዓመታት በኋላ ተዋህደዋል፡፡ ሁለቱ የመኖችም ከሰላሣ ዓመታት በኋላ ሲዋሃዱ አይተናል፡፡ ታዲያ ይህንን እያየን የምን ተስፋ መቁረጥ ነው?

እኛና ኤርትራዊያን ከመመሳሰልም አልፎ በጣም ነው የምንቀራረበው፡፡ በጣም እንዋደዳለን፡፡ ይህንን በቀላሉ ለመረዳት ኤርትራዊያንና ኢትዮጵያዊያን በዲያስፖራው ክፍለ-ዓለም የሚኖሩበትን ሁኔታ ማስተዋል ይበቃል፡፡ ወደየትኛውም የዓለም ሀገር ሄደን ብናይ ከማንም በላይ ለኤርትራዊያን የሚቀርቡት ኢትዮጵያዊያን ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ለኢትዮጵያዊያንም ከማንም በላይ የሚቀርቡት ኤርትራዊያን ናቸው፡፡ በህዳር ወር 2005 የሳዑዲ ዐረቢያ የጸጥታ ሀይሎች በኢትዮጵያዊያን ላይ የወሰዱትን በደልና ግፍ የተቀላቀላበትን ከሀገር የማባረር እርምጃ ከኢትዮጵያዊያን ጎን ቆመው ሲያወግዙ የነበሩት ኤርትራዊያን ብቻ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ባካሄዷቸው ሰልፎች ላይ ከኤርትራዊያን በስተቀር የሌላ ሀገር ዜጋ አልተሳፈተም (“ለምን ከጅቡቲ፣ ከሱዳንና ከሶማሊያ ጋር አንድነትን አትመኙም” ያልሺኝ “ነፂ ጓል ኤርትራ” ሆይ! ለጥያቄሽ መልሱን ከዚሁ ፈልጊው)፡፡

የሜዲትራኒያን ባህርን በህገ-ወጥ ጀልባዎች በማቆራረጥ ወደ አውሮጳ ሲከንፉ ባህሩ የሚበላቸው ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን ምንዱባንስ እንዴት ይረሳሉ?… ስለነርሱ በምንሰማው መጥፎ ዜና ሁለታችንም አንድ ላይ “እህ!” እያልንና በቁጭት እየተቃጠልን አይደለም እንዴ?… መርዶአቸው በአንድ ላይ እየደረሰን በአንድ ላይ ለቅሶ እየተቀመጥን አይደለም እንዴ?…

በደጉም ቢሆን መመሳሰላችንና መፈቃቀራችን ብዙ የተጻፈለት፣ ብዙ የተነገረለት ነው፡፡ ዛሬም ድረስ ያንን ሳቂታ የቤኒ አምር ወጣት የኛ ልጅ በመሆኑ ነው የምናውቀው፡፡ ዛሬም ድረስ ከኤርትራዊ ጎረቤቶቻችን ጋር ፋሲካና አረፋን በአንድነት እንታደማለን፡፡
*****
እኛ ኤርትራን የምንፈልጋት ለወደቦቿ ስንል አይደለም፡፡ እኛ ኤርትራን የምንፈልገው ሁለመናዋ ከኛ ጋር ስለሚመሳሰልና አንድ ዓይነት ስለሆነ ነው፡፡ እኛ ኤርትራን የምንፈልገው ከነህዝቧ ነው፡፡ የኤርትራ ህዝብ የኛ ህዝብ ነው፡፡ እኛ ራሳችን የኤርትራ ህዝብ ነን፡፡ ኤርትራም ኢትዮጵያ ናት፤ ኢትዮጵያም ኤርትራ ናት፡፡ ኤርትራ ወደብ ባይኖራት እንኳ ይህ አቋማችን አይቀየርም፡፡ ታሪኳ፣ ባህሏ እና ቋንቋዋ እናንተ ከምታውቁት ተቀይሯል እስካልተባለ ድረስ ስለርሷ ማለማችንን አንተውም፡፡

ህልማችን ጽኑ ነው፡፡ ወደፊት የትግበራ ምዕራፎቹን እያሰፋ የሚሄድ ነው እንጂ በእንጭጩ ተቀጭቶ የሚቀር አይደለም፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም በአፋቤት ሽንፈት ሲያጋጥማቸው በተስፋ መቁረጥ ስሜት “ቤንዚን አይቆፈርበት፤ አልማዝ አይወጣበት፣ ሰው የለበት! Nothing`” እንዳሉት እኛም ተስፋ ቆርጠን ኤርትራንና ህዝቧን የምናጥላላበት ሁኔታ በፍጹም አይከሰትም፡፡ ቢኢዝኒላህ!!

እኛ ስለትልቋ ኤርትራ ማለምን ትተን “አሰብ የኢትዮጵያ ወደብ ናት” ከሚሉት የወደብ ጥማተኞች ጎንም አንሰለፍም፡፡ ፍላጎታችን “የኢኮኖሚ እድገት” በሚባለው የማቴሪያሊስቶች ዝባዝንኬ የሚመራ ባለመሆኑ ለጥቅም ብለን ህልማችንን በመንደር ደረጃ አናሳንሰውም፡፡ ቢኢዝኒላህ!!
የእነዚህን የወደብ ጥማተኞች ቅስም ለመስበር በሚል የፖለቲካ ስሌት ተነሳስተን “የአሰብ ወደብ እጣ ፈንታ የግመሎች ውሃ መጠጫ ኩሬ ከመሆን አያልፍም” የሚል ታሪካዊ ተወቃሽነትን የሚያስከትል ቃልም አይወጣንም፡፡ ቢኢዝኒላህ!!

እኛ ኤርትራዊያንን እንደኛው አድርገን ነው የምናያቸው እንጂ አንዳንድ ብስጩዎች በሚተነፍሷው ወሬዎች ተናደን “የቅኝ-ተገዥነት ስሜት ሰለባዎች ናችሁ” በማለት አንፈርጃቸውም፡፡ በምንም መልኩ ቢሆን ኤርትራዊ ወገናችንን የሚያሳቅቅና የሚያበሳጭ ክፉ ንግግር አንናገርም፤ ክፋታችንንና የውስጥ ጥላቻችንን የሚያሳብቅ ጽሑፍም አንጽፍም፡፡ በውስጣችን ስለኤርትራ መውደም እያሰብን በምላሳችን ብቻ “አንድ ህዝቦች ነን” እያልን የምንሰብክ መናፍቃንም አይደለንም፡፡ እኛ ኤርትራንና ህዝቧን የምንወደው ከልባችን ነው፡፡ ስለነርሱ የምናልመው ህልማችንም ከልባችን ከተወረወረ የፍቅር ፍላጻ የፈነጠቀ ነው፡፡
*****
ህልማችን የቅርብ ሳይሆን የሩቅ ነው! እጅግ በጣም ሩቅ!! ይሁንና ርቀቱን ፈርተን ማለማችንን አንተውም፡፡ ዘወትር ስለውቢቷ ኤርትራና ህዝቧ ማለማችንን እንቀጥላለን!! ከሩቁና መልከ-መልካሙ ህልማችን ጋር ወደፊት!!
—-
አፈንዲ ሙተቂ
ሀምሌ 2009

 

 

Advertisement