በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያን በሀገር ቤት ላሉ ዘመድ ወዳጆቻቸው የተለያዩ የአገልግሎት ክፍያዎችን መፈፀም የሚችሉበት አገልግሎት ተጀመረ።

ባለፈው ሰኔ 21 ቀን 2009 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሆቴል በተካሄደ የፊርማ ሥነስርዓት ፋይናሺያል ቴክኖሎጂና ማስተር ካርድ ባደረጉት ስምምነት አገልግሎቱን ለመስጠት ውል ተፈራርመዋል።

በዚህም ቴክኖሎጂ በኮምፒዩተር እንደዚሁም በሞባይል ስልኮች ላይ አፕልኬሽን በመጫን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ አንድ ሰው እንደ ውሃ፣ መብራትና ስልክን የመሳሰሉ ወጪዎች በውጪ ሀገር ባሉ ዘመድ አዝማዶቹ እንዲሸፈን ማድረግ የሚችል መሆኑ ታውቋል።

የአገልግሎቱ መጀመር በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሀገር ቤት ካሉ ዘመድ አዝማዶቻቸው ጋር ይበልጥ እንዲተሳሰሩ ያደርጋል ተብሏል። በዚሁ አዲስ በተጀመረው የዲጂታል ክፍያ ዲያስፖራዎች በየትኛውም የዓለም ክፍል ሆነው በዴቢት ካርድ፣ በክሬዲት ካርድ፣ በመኒ ሞባይልና በልዩ ልዩ የባንክ አገልግሎቶች ለዘመድ አዝማዶቻቸውና ወዳጆቻቸው የቤት ወጪን መሸፈን የሚችሉ መሆኑ ታውቋል።

በዚሁ የክፍያ ሥርዓትም አንድ በውጪ ሀገር የሚኖር ሰው በሀገር ቤት ላለው ሰው የመድህን ኢንሹራንስ ክፍያን፣ የትምህርትና የህክምና ወጪን፣ እንደዚሁም የስልክ፣ የመብራትና የውሃ ወጪን መሸፈን ያስችላል ተብሏል።

ከክፍያ ፋይናሺያል ቴክኖሎጂ ጋር ስምምነቱን የተፈራረመው ማስተር ካርድ ኩባንያ አሁን ያደረገው ሥምምነት እ.ኤ.አ በ2020 በአፍሪካ ከአንድ መቶ ሚሊዮን ህዝብ በላይ በዲጂታል ክፍያ ለማስተሳሰር የያዘው አንድ እቅድ አንድ አካል መሆኑ ታውቋል።

ይሄው መረጃ በአሁኑ ሰዓት ከሶስት ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ የዓለም ክፍል የሚገኙ መሆኑን ያመለክታል። ይህ አይነቱ የቴክኖሎጂ ክፍያ ሥርዓትም ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚካሄደውን የገንዘብ ማስተላለፍ ሂደት ወደ ህጋዊውን መስመር እንዲከተል ለማድረግ የተሻለ እድል ሆኖ የሚታይ መሆኑን የክፍያ ፋይናሺያል ቴክኖሎጂ የሥራ ዓመራር ሀለፊ የሆኑት አቶ ሙኒር ዱሪ ገልፀዋል።

ምንጭ-ሰንደቅ ጋዜጣ

 

Advertisement