የሰመራ አውሮፕላን ማረፊያ ከዛሬ ጀምሮ ለቀጣዮቹ 21 ቀናት አገልግሎት እንደማይሰጥ ተገለጸ

በእድሳት ላይ ሚገኘው የሰመራ አውሮፕላን ማረፊያ ከዛሬ ጀምሮ ለቀጣዮቹ 21 ቀናት አገልግሎት መስጠት ማቋረጡን የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድም ተክሉ ለኢዚአ እንደተናገሩት በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የአየር ማረፊያዎችን ደረጃ የማሻሻልና ተደራሽ የማድረግ ሥራ ትኩረት የተሰጠው ቁልፍ ተግባር ነው።

በእዚህም በጠጠር ደረጃ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው የሰመራ አየር ማረፊያ ወደ ኮንክሪት አስፓልት እንዲያድግ በመደረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

እየተካሄደ ባለው የእድሳት ሥራ ምክንያት ለቀጣዮቹ 21 ቀናት አየር ማረፊያው አገልግሎት የማይሰጥ በመሆኑ ተጋዦች የኮምቦልቻንና መቀሌን አየርማረፊያዎች በአማራጭነት ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

በአየር ማረፊያው የማሻሻያ ሥራ ደረጃውን የጠበቀ የመንገደኞች ማረፊያ ተርሚናል ግንባታ ሥራ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተከናወነ ይገኛል።

ከሁለት ዓመት በፊት ግንባታው የተጀመረው የአውሮፕላን መንደርደሪያ ኮንክሪት አስፓልት 2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 60 ሜትር ስፋት አለው።

ከአውሮፕላን መንደርደሪያ ሜዳው ከግማሽ በላይ የሚሆነው በአሁኑ ወቅት ግንባታው ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን ቀሪው የአውሮፕላን መንደርደሪያ የመጀመሪያ ደረጃ አስፓልት መልበሱን አቶ ወንድም አመልክተዋል።

ቀሪ ሥራዎችን በቀጣዮቹ 21 ቀናት ሙሉ ለሙሉ በማጠናቀቅ አየር ማረፊያው ሥራውን እንዲጀምር የሚደረግ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከሦስት ወር በፊት ግንባታው የተጀመረው ተርሚናል በአሁኑ ወቅት ሃያ በመቶ መጠናቀቁን አስታውሰው፣ ተርሚናሉን ክልሉ በቀጣይ ዓመት ለሚያስተናግደው 12ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ለማድረስ በሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ተርሚናሉ የክልሉን ከፍተኛ ሙቀት ለመቋቋም በሚችል ዲዛይንና የሕብረተሰቡን ባህል በሚወክል መልኩ የተዘጋጀ ሲሆን በአንድ ጊዜ 150 መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም አለው።

ከእዚህ በተጨማሪ ልዩ መስተንገዶ የሚያስፈልጋቸው እንግዶች የሚስተናግዱበት ክፍሎች እንዲኖሩት መደረጉን ኃላፊው አቶ ወንድም ገልጸዋል።

የአየር ማረፊያውን ደረጃ ማሳደግ ስራዉ ተጠናቆ ለአገልገሎት ሲበቃ አሁን እያስተናገደ ከሚገኘዉ “Q-400” አውሮፕላን በተጨማሪ “ቦይንግ 737” አውሮፕላኖችን ማስተናገድ ይችላል።

ይህም የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራቱን ከማሻሻል ባለፈ እያደገ የመጣውን የተጓዥ ቁጥር በአግባቡ ለማስተናገድ የጎላ ፈይዳ እንደሚኖረው ነው የገለጹት።

ኤርፖርቱ ደረጃውን እንዲያድግ መደረጉ ለክልሉ ሕብረተሰብ ዘረፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ እንደሚያበረክትም አመልክተዋል።

የሰመራ ኤርፖርት የበረራ አገልግሎት ሥራውን ታህሳስ 2006 ዓ.ም እንደጀመረ ይታወቃል።

ምንጭ፡ኢዜአ

 

Advertisement