ንግድ ባንክ፤ 150ሺ ብር ተጭበርብረው ለተወሰደባቸው ደንበኛው ምላሽ አለመስጠቱ አነጋጋሪ ሆኗል

 

ከድርጅቴ ሒሳብ ቋት ገንዘብ የወጣበት ቼክ ቁጥር ድርጅቴ አያውቀውም-ተበዳይ

ንግድ ባንክ፣ ከመሠረት ደፋር ቅርንጫፍ ባንክ ከኤኢ አለሜት ኢትዮጵያ አስጎብኝና ከመኪና ኪራይ አገልግሎት አቅራቢ ድርጅት እ.ኤ.አ. በ25/11/2016 ከሒሣብ ቁጥር 1000113007552 በቼክ ቁጥር 11504411 በአቶ ቶማስ ሲሳይ በሚባል ስም ብር 150,000 /አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ ብር/ ከድርጅቱ እውቅና ውጪ ተጭበርብሮ መከፈሉ ታውቋል።

የድርጅቱ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ እንደተናገሩት፣ “ከድርጅቴ ከሒሳብ ቋት ገንዘብ የወጣበት ቼክ ቁጥር ድርጅቴ የማያውቀው ነው። እንዲሁም ከመሠረት ደፋር ቅርንጫፍ በድርጅቴ ስም ባንኩ የሰጠኝም ቼክ አይደለም። ክፍያው ግን የተፈጸመው ከድርጅቴ የሒሳብ ቋት ጋር በማገናኘት ነው። ቼክ ከዚህ ቅርንጫፍ ተሠርቆ የወጣ እንጂ እኔ ወስጄ እየተጠቀምኩበት ካለው ቼክ ላይ አይደለም። ሌላው አቶ ቶማስ ሲሳይ የሚባል ሰው ፈጽሞ አላውቅም። ባንኩ በነበረው አሰራርም ይህንን ያህል መጠን ገንዘብ ከድርጅቴ ቋት ሲወጣ ደውለው ቢያንስ እንዲከፈል ሊያሳውቁኝ በተገባ ነበር። የሚገርመው ላለፉት ሰባት ወራት ተመላልሼ ባንኩን ብጠይቅም የተሰጠኝ መፍትሄ የለም” ብለዋል።

“የቅርንጫፉ ሥራአስኪያጅ ምን ምላሽ ሰጡ? የንግድ ባንክ ፕሬዝደንትን ማነጋገር አልቻሉም?” በሚል ለአቶ አለሙ ላቀረብንላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ “የቅርንጫፍ ሥራአስኪያጅ አቶ ሽብሩን አነጋግሬው ነበር። የባንኩንም መዝገብ ሁለታችንም አይተነዋል። በተጠቀሰው ቁጥር ቼክ ተሰርቶ ከባንኩ ወጪ ሆኗል። ማን እንዳወጣው አይታወቅም። ከባንኩ የተሰጠኝ የድርጅቴ ቼክ በእኔ እጅ እንደሚገኝ አሳይቻለሁ። ተጭበርብሮ በወጣው ቼክ ከድርጅቴ የሒሳብ ቋት ከእኔ እውቅና ውጪ መሰረቁን ተማምነናል። ባንኩ ከሰጠኝ የቼክ ቁጥር ጋርም አነፃፅረን ተመልክተናል። ባንኩ በተጭበረበረው ቼክ ቁጥር የሰጠኝ የባንክ ኖት እንደሌለ ሁሉም ያዩት ጉዳይ ነው።” ሲሉ አስታውቀዋል።

የመሰረት ደፋር ቅርንጫፍ ሥራአስኪያጅ አቶ ሽብሩ አነጋግረናቸው የሰጡን ምላሽ፣ “ጉዳዩ በፍርድ ቤት የተያዘ በመሆኑ አስተያየት አልሰጥም” ብለው ነበር። “ጉዳዩ በፍርድ ቤት የተያዘ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሥነ ምግባር መኮንን የተላከ ነው። ስለዚህ እርስዎ የሚያውቁትን ቢገልጹልን?” ብለን ለጠየቅናቸው ጥያቄ “ደንበኛችን የባንኩን ሕግ ክፍል ሲያናግሩ እንደነበር አውቃለሁ። ከዚህ ውጪ በምርመራ ላይ ባለጉዳይ ምላሽ አልሰጥም” ብለዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥነ ምግባር መኮንን አቶ ግርማ በበኩላቸው፣ “ጉዳዩን እንደሚያውቁት ገልጸውልን፣ በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ፊርማ አጭበርብሮ ክፍያ በወሰደው ግለሰብ ላይ ልዩ ምርመራ እየተደረገ ነው። ገንዘብ ላለመክፈል ፈልገን አይደለም። መረጃ ለፌደራል ፖሊስ አቅርበናል። የምርመራው ውጤት ማግኘት የግድ ይላል” ብለዋል።

“ደንበኛው በዚህ ጉዳይ ሰባት ወር ድረስ መጉላለት አለባቸው ወይ? ባንኩ በራሱ መንገድ ምርመራውን ቀጥሎ ለደንበኛችሁ ምላሽ መስጠት አይጠበቅባችሁም ወይ?” ለተባሉትም አቶ ግርማ በሰጡት ምላሽ፣ “አጨበርብሮ ወስዷል የተባለው ሰውዬ ተገኝቶ ሲጠየቅ ነው ሁሉን ነገር ማወቅ የሚቻለው። ሰውየው ሲያዝ ቼኩን ሰጥተውኝ (ደንበኛው) ነው ሊል ይችላል” ሲሉ ሞግተዋል።

“በደንበኛችሁ ስም ያልተመዘገበ የቼክ ቅጠል ቁጥር ተጠቅሞ ገንዘብ ወስዷል ነው የተባለው። ለደንበኛችሁ መዝግባችሁ ባልሰጣችሁት የቼክ ቅጠል ቁጥር እንዴት አደናጋሪ ሁኔታ ሊፈጥር ቻለ?” ለሚለው በሰጡት ምላሽ “በቼኩ ላይ ያረፈው ፊርማ ከደበኛችን ፊርማ ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ በፎረንሲክ እንዲታይ ለፌደራል ፖሊስ ሰጥተናል። ቼኩም ላይ የሰፈረው ስም የደንበኛችን ነው። ስለዚህም በቼክ አጭበርብሮ ገንዘብ ወስዷል ከተባለው ሰው ጋር ደንበኛችን ግንኙነት ይኑራቸው፣ አይኑራቸው አሁን ለማወቅ አይቻልም። በቼኩም ላይ የተመዘገበው ቁጥር የደንበኛችን ነው። በዚህ ጉዳይ የተጠረጠሩ ሰዎች ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው። በደንበኛችን ላይም ምርመራ ተደርጓል። በድርጅቱ ሠራተኞች ላይም ምርመራ እየተደረገ ነው” ሲሉ አቶ ግርማ ገልጸዋል።

በባንክ ሥራ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ለሰንደቅ እንደገለጹት፣ “ደንበኞች ገንዘብ በአደራ ነው በባንክ የሚያስቀምጡት። በአደራ ያስቀመጡትን ገንዘብ በጠየቁ ጊዜ የማግኘት መብት አላቸው። ይህንን የደንበኞችን መብት ባንክ ማረጋገጥ ካልቻለ ቸልተኛ ሆኗል ተብሎ ይወሰዳል። ስለዚህም ከደንበኞች ላይ ተጭበርብሮ ገንዘብ ከባንክ ከተወሰደ፣ ወንጀለኛው ተገኘም፣ አልተገኘም፤ በሕጋዊ መንገድ ተይዞ ተጣራም፣ አልተጣራም፤ የደንበኞችን ገንዘብ ወደ ቋታቸው መልሶ ነው ወደ ማጣራት የሚገባው። ወንጀለኛውን ተፋርጄ ገንዘብ አስመልሼ እከፍላለሁ የሚል ምላሽ ከባንክ የሚሰጥ ወይም የሚጠበቅ አይደለም። ምክንያቱም ተጭበረበረ የሚባለው ቼክ ከደንበኛው ካልወጣ፤ የደንበኛውን ፊርማ የራሱ መሆኑን ማረጋገጥ በማይችልበት ሁኔታዎች ውስጥ ደንበኛውን ያስቀመጠውን ገንዘብ አለውጣ ውረድ ሊከፍለው ይገባል። እኛም የምንሰራበት አካሄድ ተመሳሳይ ነው።

በተለምዶም ከ50ሺ ብር በላይ ገንዘብ ወጪ ሲጠየቅ ብዙውን ጊዜ ወደ ደንበኞች እየተወደለ እንዲያውቁት ይደረጋል። ፈቃዳቸው መሆኑ ሲረጋገጥ፣ ወዲያው ክፍያ ቼኩን ይዞ ላመጣው ሰው ይከፈለዋል። ስለዚህ የደበኛውን ገንዘብ እንደመያዣ በመያዝ ባንኩ በፖሊስ ሥራ ገብቶ ሊከለክለው አይገባም። ባንኩ በራሱ ችግር ደንበኛውን ተጠያቂ አድርጎ መያዝ ተገቢ አይደለም። ሰባት ወር የሚያስጠብቅ ምርመራም አይደለም” ሲሉ አካሄዱን ተችተዋል።

አቶ አለሙ በበኩላቸው ለወራት በፌደራል ፖሊስ የሙስና ወንጀሎች ምርመራ ቢሮ ስመላለስ ቆይቼ የተገነዘብኩት ከባንኩ የሚሰጠኝ ምክንያት መሰረተ ቢስ መሆኑን ነው። ምክንያቱም ፌደራል ፖሊስ ጉዳዩን አጣርቶ ወንጀለኛውን ቢያገኘውም ወይም የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን ቢደርስበትም የሚያሳውቀው ለመንግስት አቃቤ ሕግ እንጂ ለባንኩ አይደለም። በዚህ መካከል በገዛ ገንዘቤ መጉላላቴ የሚያሳዝን ነው። የባንኩ ከፍተኛ ኃላፊዎች ችግሬ በመስማት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡኝ “ደንበኛ ንጉስ ነው” በሚለው ታሪክ በማይሽረው በአገልግሎት ቋንቋ እጠይቃለሁ ብለዋል።

ምንጭ፥ ሰንደቅ ጋዜጣ

Advertisement