ድሬ የኚህ ሰው ውለታ አለብሽ!! አቶ መርሻ ናሁ ሰናይ።

ከጅቡቲ የተነሳው የባቡር ሀዲድ እ.ኤ.አ. በ1902 ዛሬ ድሬዳዋ ካለችበት ቦታ ሲደርስ በአቶ መርሻና በፈረንሳዊው ሌዎን ሸፍነ መሪነት አዲስ ከተማ እንዲቆረቆር ትእዛዝ ተሰጠ።
የቦታውም ስም መጀመሪያ አዲስ ሐረር ተባለና ትንሽ ቆይቶ ግን ድሬዳዋ የሚል ስያሜ ተሰጠው። በአፋን ኦሮሞ ድሬ ማለት ሜዳ ሲሆን ዳዋ ማለት ደግሞ መድሃኒት እንደማለት ነው።

በዚያው ዓመት አቶ መርሻ ናሁ ሰናይ የድሬዳዋና አካባቢው የመጀመሪያ አስተዳዳሪ ሆነው ተሾሙ። ብዙም ሳይቆይ በምድር ባቡር ኩባንያው ባልደረቦችና በበርካታ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ድካም ድሬዳዋ ቶሎ ቶሎ መገንባት ጀመረች። በአጭር ጊዜ ውስጥም ዘመናዊ የሆነ ከተማ ተቋቋመ።

አቶ መርሻ በከተማውና አካባቢው አስተዳዳሪነት እስከ 1906 እ.ኤ.አ. ድረስ ካገለገሉ በኋላ ለሚቀጥሉት ሃያ ዓመታት ማለትም ጡረታ እስከወጡብት ጊዜ ድረስ የኢሳ ግዛቶች እና የባቡር ሀዲዱ ጥበቃ ሀይል ኃላፊ በመሆን ሰርተዋል። በልጅ ኢያሱ ዘመነ ስልጣን ለአጭር ጊዜ ተሽረው የነበረ ሲሆን ኢያሱ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ወደ ቦታቸው ተመልሰዋል፡

መርሻ ናሁሰናይ እንደ አውሮጳ አቆጣጠር በ1850 መጀመሪያ ገደማ በአንኮበር አካባቢ በሽዋ ተወለዱ። እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰም በአቅራቢያቸው ከሚገኝው ወላጅ አባታቸው ከሚያገለግሉበት ቤተክርስቲያን ገብተው መሰረታዊ የሃይማኖትና ቀለም ትምህርትን እንደቀሰሙ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየ የቤተሰብ አፈ ታሪክ ያመለክታል።

መርሻ የወጣትነት ጊዜያቸውን በአባታቸው እርሻና በቤተክርስቲያን አካባቢ በመማርና በመርዳት አሳልፈዋል። ከቦታ ቦታም እየተዘዋወሩ ሰፊ ዕውቀትንና ልምድን አካብተዋል። በጎልማሳነት ዕድሜያቸው ምን አይነት ባህርይ እንደነበራቸው ዝርዝር መረጃ እስካሁን አልተገኘም። ሆኖም ግን ከልጅነታቸው ጀምሮ የተለያዩ ነገሮችን ለመማርና ለመሞከር ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበራቸውና ብርቱ ጥረት እንዳደረጉ ይነገራል፡፡

የዓፄ ምኒልክና የራስ መኮንን አማካሪና የቅርብ ረዳት በመሆንም በወቅቱ ሀገራዊና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ላይ ተሳታፊ ለመሆን እድል አግኝተዋል። አቶ መርሻ ዘመናዊ ዕውቀትን የቀሰሙ፤ የፈረንሳይኛ ቋንቋን ያጠኑ፤ ስለአውሮጳ ታሪክና ባህል ሰፊ ዕውቀት የነበራቸውና በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም ለመታወቅ የበቁ አስተዋይ ሰው ነበሩ።

ድሬ የኚህ ሰው ውለታ አለብሽ!!

ድሬ ስትጠቀስ ስማቸውም አብሮ ከሚነሳ የጠሃይ መውጫ ልጆች መካከል
ተወዳጅ ድምጻዊ አሊ ቢራ፣ ሐኪሙ ፕ/ር አስራት ወልደየስ፣ ባዮ ኬሚስቱ መምህር ዶ/ር ጌታቸው ቦሎዲያ፣ ዶ/ር አብዱል መጂድ ሁሴን፣ ባለሀብቱ ኦክሲዴ፣ ገጣሚና ደራሲ ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ፣ እግር ኳስ ተጫዋቹ ሚግ፣ ተወዳጆቹ ጋዜጤኞች ጳውሎስ ኞኞ እና ደምሴ ዳምጤ እንዲሁም ሌሎች ከድሬ ምድር በቀሉ፡፡

 

ምንጮች
^ ታዴዎስ አሰበወርቅ Mersha Nahusenay bio in English)
^ Richard Pankhurst. “The beginnings of Ethiopia’s modernisation”. 2003.
^ Getahun Mesfin Haile (2003). “Dire Dawa: Random thoughts on a centenary”. Addis Tribune.
^ ገዛህኝ ይልማ (ታህሳስ 2000 ዓ.ም.). “ድሬዳዋ የምዕተ ዓመት ጉዞ”. ድሬ መጽሔት (ልዩ እትም).

 

 

 

Advertisement