ኢትዮጵያና ሩሲያ በተለያዩ ዘርፎች በጋራ ለመስራት ከስምምነት ደረሱ::

                      

ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በተለያዩ መስኮች በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን አስታወቁ።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከሩሲያ አቻቸው ሰርጌይ ላቭሮቭ ጋር በሞስኮ ተገናኝተው መክረዋል።

ከውይይታቸው በኋላ በሰጡት የጋራ መግለጫም ሀገራቱ በተለያዩ ዘርፎች በጋራ ለመስራት ከስምምነት መድረሳቸውን ነው ያስታወቁት።

ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በተለይም በሀይል እና በመሰረተ ልማት ግንባታ ዘርፍ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ገልጸዋል።

ሩሲያ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ ከውሃ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫዎች ግንባታ እና የማዘመን ስራ ላይ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላት የገለጸች ሲሆን፥ “ጂ.ቢ.ፒ ግሎባል ሪሶርስ” የተባለ የሀገሪቱ ኩባንያ በአሁኑ ጊዜ በምስራቅ የኢትዮጵያ ክፍል “በሃይድሮ ካርበን” ፍልጋ ላይ ተሰማርቶ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም ባሳለፍነው መጋቢት ወር በአዲስ አበባ የተካሄደው የኢትዮ-ሩሲያ የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሳይንሳዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመግባቢያ ስምምነት በተፈራረሙባቸው ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ከስምምነት መድረሳቸውን አስታውቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ባለፈው ሳምንት በሁለቱ አገራት መካከል በተፈረመው የአቶሚክ ሃይልን ለሰላማዊ አላማዎች የመጠቀም ስምምነት ዙሪያም መወያየታቸውን ነው የገለፁት።

በወታደራዊ ጉዳዮች ዙሪያም በቴክኒክ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች፣ በወታደራዊ ሳይንስ እና ትምህርት ዙሪያ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን አስታውቀዋል።

እንዲሁም በሩሲያ የሚማሩ የኢትዮጵያ ተማሪዎችን ቁጥር ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

በዓለም አቀፍ ሰላም እና ፀጥታ ዙሪያ ሽብርተኝነትን በመዋጋት፣ የአደንዛዥ እፅን ዝውውርን በማስቆም እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት መስማማታቸው በመግለጫቸው ላይ ተመልክቷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በመግለጫው ወቅት እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር በሀይል ልማት፣ በማዕድን እና በሌሎች ዘርፎች የምትሰራቸው ስራ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ትፈልጋለችም ብለዋል።

“በርካታ የሩሲያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በማዕድን እና ሀይል ዘርፍ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ እንገልጋለን፤ ለዚህም መመንግስት ማበረታቻዎችን ያደርጋል” ብለዋል።

ዶክተር ወርቅነህ አያይዘውም፥ ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በህዝብ ለህዝብ፣ በባህል እና በተለያዩ ዘርፎች ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ናቸው ብለዋል።

የሩሲያ ህዝብ እና መንግስት በችግራችንም ይሁን በልማታችን ጊዜ ከጎናችን ነበሩ ያሉት ዶክተር ወርቅነህ፥ በዚህ ሁለንተናዊ ግንኙነት ላይም ወደፊት ከፍተኛ አመኔታ አለን ሲሉም ተናግረዋል።

ዶክተር ውርቅነህ በቀጣይ ዓመት የኢትዮጵያ እና የሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረበት 120ኛ ዓመት እንደሚከበር እና ይህም በአፍሪካ ባለረጅም እድሜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደሆነ ነው ያስታወቁት።

120ኛ ዓመት የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በዓልንም በቀጣዩ ዓመት በባህላዊ እና ሌሎች ስነ ስርዓቶች እንደሚከበር በዚሁ ወቅት ይፋ አድርገዋል።

በኢትዮጵያ እና በሩሲያ መካከል ያለው ግንኙነት የበለጠ እንዲያድግም የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በቀጣይ ዓመት በኢትዮጵያ ጉብኝት እንዲያደርጉ ጋብዘዋል።

የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በዶክተር ወርቅነህ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ የቀረበላቸውን ገብዣ በደስታ እንደሚቀበሉ ገልጸው፥ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ መስኮች የመስራት ፍላጎች እንዳላት አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በተለያዩ የዓለም አቀፍ መድረኮች ያላትን ሚዛናዊ አቀራረብ ያደነቁት ሰርጌይ ላቭሮቭ፥ ሀገሪቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል መሆኗ እና ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆነው መመረጣቸው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላት ተሰሚነት መጨመሩን ያሳያል ብለዋል።

ሀገራቸው ሽብርተኝነትን ከመዋጋት ጀምሮ በሌሎች ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይም ከኢትዮጵያ ጋር የመስራት ፍላጎት እንዳላት ሰርጌይ ላቭሮቭ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ እና የሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ረጅም ዓመት ማስቆጠሩን የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፥ ግንኙነቱ የተጀመረበት 120ኛ ዓመትን በተለያዩ ስነስርዓቶች ለማክበር ተስማምተናል ብለዋል።

ምንጭ፦www.mid.ru

Advertisement