የልብ ህመምና በጭንቅላት ውስጥ የደም መፍሰስ ተጋላጭነትን ለመቀነስ – Ways to Reduce Your Risk of Heart Disease and Stroke

                         

የሚከተሉት የህይዎት ዘይቤ ጤንነትዎን ለመጠበቅና በጤና ለመሰንበት ከፍ ያለ ጠቀሜታ አላቸው።

ለራስ ጊዜ መስጠት፣ ጫና ያልበዛበት ህይዎት መምራት፣ አመጋገብ እና ሌሎችም ጉዳዮች ጤንነትን በመጠበቅ ረገድ የራሳቸው አስተዋጽኦ አላቸው።

የጤና ባለሙያዎችም ከአመጋገብ ጀምሮ ራስን በመንከባከብ በጤና መቆየት እንደሚቻል ያነሳሉ።

ባለሙያዎቹ የልብ ህመም ተጋላጭነትን እና በጭንቅላት ውስጥ ደም የመፍሰስ አጋጣሚን ለመቀነስ የሚረዱ ምክር ሃሳቦችንም አስቀምጠዋል።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፦ በቀን ውስጥ ለ30 ደቂቃዎች ያክል አነስተኛ እና መካከለኛ የሚባሉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ለጤና ጠቃሚ መሆኑን ነው የሚመክሩት።

እንደ ሶምሶማ፣ ገመድ ዝላይ እና ዋና የመሳሰሉ ቀላል የአካል ብቃት አንቅስቃሴዎችን በማድረግ የልብ ህመም ተጋላጭነትንና በጭንቅላት ውስጥ ደም የመፍሰስ አጋጣሚን መቀነስ ይቻላል።

ይህን በሳምንት ለአምስት ቀናት መስራት እና ሁለቱን ቀን ደግሞ እንደ ክብደት ማንሳት ያሉ ትንሽ ጫና ያላቸውን ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች መከወን።

የኮሊስትሮል መጠንን መቀነስ፦ ለከፍተኛ ውፍረት የሚዳርገውን የኮሊስትሮል መጠንን በአግባቡ መቀነስ መቻል።

በዚህ ሳቢያ አላስፈላጊ ውፍረት ከተጋለጡ በልብ ህመም የመጋለጥ እድልዎና በጭንቅላት ውስጥ ደም የመፍሰስ አጋጣሚ ሊከሰት ይችላል።

ይህን ደግሞ የኮሊስትሮል መጠንን በማስተካከልና አላስፈላጊ ውፍረትን በመቀነስ ማስወገድ ይቻላል።

አመጋገብ፦ ጤናማ የሚባሉ አመጋገቦችን መከተልም ለዚህ እንደሚረዳ ነው ባለሙያዎቹ የሚናገሩት።

ለዚህም አትክልትና ፍራፍሬዎች፣ ጥራጥሬ፣ አሳ፣ በፕሮቲን የበለጸጉ ምግቦችን እንዲሁም የዶሮ እና የጥጃ ስጋዎችን መመገብ።

ከዚህ ባለፈ ግን ተቀነባብረው የሚሸጡ ምግቦችን አለመመገብ የመጀመሪያ ምርጫዎ ሊያደርጉ ይገባል።

አልኮል መጠጦችን አለማብዛት፦ የደም ግፊት፣ የልብ ህመም እና የጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ አጋጣሚዎች በዚህ ሳቢያ ሊከሰቱ ስለሚችሉ ከዚህ ቢርቁ ይመረጣል።

ጣፋጭ ነገሮችን መቀነስ፦ ምናልባት ቼኮሌት አፍቃሪ ከሆኑም በጣም አልፎ አልፎ መመገብና ስኳርና ጨው የበዛባቸውን ምግቦችም ከገበታ ማስወገድ።

ሲጋራ አለማጨስ፦ ሲጋራ አጫሽ መሆን በሂደት ለልብ ህመምና ለጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ የማጋለጥ አቅም አለው።

እናም በተቻለ መጠን ሲጋራ ከማጨስ መቆጠብ ይኖርብዎታል።

እንግዳ ስሜት ሲሰማዎት ሃኪምዎን ያማክሩ፦

ያልተለመደ እና ወጣ ያለ ስሜት ከተሰማዎት ወደ ሃኪም ቤት በመሄድ ሃኪም ማማከርን አይዘንጉ።

የትንፋሽ መቆራረጥ፣ የልብ ምት መጨመር፣ ከፍተኛ ድካም፣ በመንጋጋ ወይም ጀርባ አካባቢ የተለየ የህመም ስሜት፣ ማስመለስ፣ መጠኑ የበዛ የአፍንጫ ፈሳሽ፣ ከፍተኛ ላብ እና የጉንፋን አይነት የህመም ስሜቶች ሲሰሙ ወደ ሃኪም ቤት ማምራት።

እንደ ባለሙያዎቹ ገለጻ እነዚህ ስሜቶች የበሽታዎቹ ምልክቶች ሊሆኑ ስለሚችሉ በፍጥነት ሃኪም ማማከር ያስፈልጋል።

ምናልባት ይህ ሁሉ ሆኖ ሃኪም መድሃኒት እንዲወስዱ አዞልዎት ከሆነም አለማቋረጥና በአግባቡ መውሰድ ይኖርብዎታል።

መውሰድ እንዳይችሉ የሚያደርግዎት ምክንያት ካለም ሃኪሙን ማማከር አይርሱ።

በቂ እንቅልፍ ማግኘት እና በተለያዩ ቪታሚኖች የበለጸጉ ምግቦችን መመገብም አይዘንጉ።

ምንጭ፦ webmd.com

Advertisement