የጡት ወተት ውስጥ ያለው ንጥረ ነገርና ካንሰርን የመከላከል አቅሙ…

                                       

በተለይም ለህጻናት ጤንነት እጅግ በጣም ብዙ ጠቀሜታዎችን እንዳሉት የሚነገርለት የጡት ወተት አሁን ደግሞ በህክምናው ዓለም አዲስ ተስፋን ይዞ መምጣቱ እየተነገረ ነው።

አዲስ የተገኘ የጥናት ውጤት እንደሚያመለክተው በጡት ውስጥ የሚገኘው እና “ሀምሌት” የሚል ቅፅል ስም ያለው ንጥረ ነገር የካንሰር እጢ ህዋስን የመግደል አቅሙ ከፍተኛ ነው።

የስዊድን ሉንድ ዩኒቨርሲቲ ተመራመናሪዎች ሀምሌት ባለው ጠቀሜታ ላይ ጥናት ያደረጉ ሲሆን፥ በተለይም የሽንት ፊኛ ካንሰርን በመከላከሉ ረገድ ተስፋ የተጣለበት ውጤት ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።

በፊኛ ካንሰር በተጠቁ ሰዎች ላይ በተደረገ ሙከራም፥ የሀምሌት ንጥረ ነገርን በመርፌ መልክ የተወጉ ሰዎች በጥቂት ቀናት ውስጥ የሞቱ የካንሰር ህዋሶች ከሽንታቸው ጋር ተቀላቅሎ ሲወጣ ተስተውሏል።

የጡት ወተት ንጥረ ነገር የካንሰር ህዋሶችን ብቻ ያጠቃል የተባለ ሲሆን፥ ይህም ለካንሰር ህክምና ጥቅም ላይ ለሚውሉትንና የካንሰር ህዋሶችን ሲገድሉ ሌሎች ህዋሶች ላይ ጉዳት ያደርሳሉ ለሚባሉት የኬሞቴራፒ እና ራዲዮቴራፒ ህክምናዎች የተሻለ አማራጭ መሆኑም ነው የተነገረው።

የኢሚዩኖሎጂ ፕሮፌሰር ካትሪና ስቫንቦርግ፥ “በአንቲ ባዮቲክስ” ዙሪያ ምርምር በማድረግ ላይ እያሉ በድንገት የጡት ወተት ንጥረ ነገር ካንሰርን ከመከላከል አንጻር ጥቅም እንዳለው ማግኘታቸውም ተነግሯል።

“አሁን የተገኘው የጥናት ውጤት በጣም አስገርሞናል፤ የጡት ወተት ንጥረ ነገሩን በምንቀላቅልበት ጊዜ የካንሰር ህዋሶቹ ሲሞቱ መመልከት ችለናል፤ ይህ በጣም ታላቅ ግኝት ነው” ሲሉም ፕሮፌሰር ካትሪና ተናግረዋል።

እንደ ተመራማሪዎች ገለጻ በጡት ወተት ውስጥ የሚገኘው እና “ሀምሌት” በመባል የሚጠራው ንጥረ ነገር ከሽንት ፊኛ ካንሰር በተጨማሪም የአንጀት ካንሰር እና ሌሎች የካንሰር አይነቶችን የመከላከል አቅም ሊኖረው እንደሚችልም ጠቁመዋል።

አሁንም ቢሆን በጡት ወተት ውስጥ በሚገኘው ሀምሌት ንጥረ ነገር ላይ የሚደረገው ምርምር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

ምንጭ፦ www.independent.co.uk

Advertisement