ኮርያ ላይ ሆኜ አድዋን ሳስባት

                       
ዋና ከተማ ሶኡል፣ ናምዮንግ ዶንግ፣ ዮንግሳን-ጉ (29 Itaewon-ro, Namyeong-dong, Yongsan-gu, Seoul) በሚገኘው የጦርነት መታሰቢያ ሙዝየም ግድግዳዎች ላይ በኮርያ ጦርነት ወቅት ከመላው ዓለም ተሰባስበው ሲዋጉ የተሠዉ ወታደሮች ስም ዝርዝሮች ተጽፈዋል፡፡ በዚህ ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያ 121 ወታደሮቿን መሠዋቷ ተገልጧል፡፡ ከሁሉም ሀገሮች ብዙ ወታደሮችን ያሰለፈችውና ብዙ ወታደሮቿንም ያጣችው አሜሪካ ናት፡፡ የአሜሪካ ወታደሮች ዝርዝር በየግዛታቸው ረዥሙን ግድግዳ በሁለት እጥፍ ሞልቶታል፡፡
ይህን ሙዝየም ስጎበኝ ሁለት ነገሮች በሐሳቤ ይመጡ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን በታሪኳ እጅግ ብዙ ጦርነቶችን አድርጋለች፡፡ በጦርነቱ ተጎድተናል፤ በጦርነቱም ተጠቅመናል፡፡ የሕይወት ጥፋት፣ የንብረት ጉዳት ደርሶብን፣ ማኅበራዊ ቀውሶችንም በተሸክመን የተጎዳነውን ያህል ሀገራችንን ከጠላት ጠብቀን በማወቆየታችን ነጻነት የሚያስገኘውን መንፈሳዊና ቁሳዊ ጥቅምም አግኝተናል፡፡ በነጻነታችን ላይ ቆመን ሌሎች ነጻ እንዲሆኑም ታግለናል፡፡ ጦርነቶቻችን የዛሬዋን ሀገራችንንና የዛሬዎቹን ሕዝቦቻችንን አሁን ባሉበት መልክ ሠርተዋቸዋል፡፡ ይህ ሁሉ ቢሆንም የኢትዮጵያን የጦርነት ታሪክ የሚያሳይ አንድም የጦርነት መታሰቢያ ሙዝየም ግን የለንም፡፡
በኢትዮጵያ ምድር የነበሩ ጦርነቶችን፤ ጦርነቶቹ በሀገሪቱ ላይ ያደረሱትን አዎንታዊና አሉታዊ ተጽዕኖዎች፣ በጦርነቶቹ የነበረውን አሰላለፍ፣ ትጥቅ፣ ስንቅ፣ ወታደራዊ አደረጃጀት፣ የጦርነቱ መሪዎችንና ተሳታፊዎችን፣ የተሠዉ ጀግኖቻችንን፣ የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን፣ የወደመ ንብረታችንን፣ የተገኘ ነጻነታችንን ሊያሳይ የሚችል ብሔራዊ ሙዝየም ያስፈልገን ነበር፡፡
በዚህ ሙዝየም ከጦርነት ጋር የተያያዙ መዛግብት ይቀመጡበታል፣ ከጦርነት ጋር የተያያዙ ቅርሶች ይሰበሰቡበታል፣ ከጦርነት ጋር የተያያዙ ፎቶዎች፣ ሥዕሎችና ቪዲዮዎች ይታዩበታል፤ ጀግኖቹ ይከበሩበታል፤ አጥፊዎቹ ይወቀሱበታል፤ ሀገርን ሀገር አድርጎ ለማቆየት የተከፈለው መሥዋዕት ይዘከርበታል፤ ካለፈው ትምህርት ይወሰድበታል፤ለወደፊቱ ጥንቃቄ ይደረግበታል፡፡ የጦርነት መታሰቢያ ሙዝየም ስለሌለን ከጥንት እስከ ዛሬ አባቶቻችን እንዴት ተጋድለው፣ በምን ተጋድለው፣ ምን ለብሰው ተጋድለው፣ ምን ሰንቀው ተጋድለው፣ እንዴት ዘምተው ተጋድለው፣ እንዴት ተደራጅተው ተጋድለው ይህችን ሀገር እንዳቆዩዋት መልክ ባለው ደረጃ ታሪኩን ለመዘከር አልቻልንም፡፡ የቀድሞ መሣሪያዎቻችን እየጠፉ፣ የቀድሞ ወታደራዊ ማዕረጎች እየተረሱ፣ የቀድሞ የስንቅ ማዘጋጃ ሞያዎችና ዕቃዎች እየቀሩ፣ የቀድሞ የጦርነት ዐውዶች ለሌላ ተግባር እየተቀየሩ ይገኛሉ፡፡ 
ካለፈው ለመማር ባለመቻላችን ጦርነቶችን ደጋግመናቸዋል፤ ዛሬም ወደ ጦርነት የሚያመራው መንፈሳችን እንዳለ ነው፡፡ ለግጭቶች መፍቻ የሚሆኑ በቂ መንገዶችንም አልተለምንም፡፡ ካለፈው በሚገባ የማይማር የትናንቱን ስሕተት ለመድገም የተረገመ ነው ይባላልና፡፡
ሌላው ጉዳይ ደግሞ ለሀገራቸው ሲሉ መሥዋዕት የከፈሉ ጀግኖቻችን ጉዳይ ነው፡፡ ለመሆኑ በአድዋ ጦርነት የተሰለፉ ጀግኖች ስም ዝርዝር ይታወቃል? ተጽፎ ሊገኝበት የሚችል ይፋዊ መዝገብስ አለን? አድዋን ከተራራነት ወደ ታሪካዊ ሙዝየምነት ሳንቀይረው 115 ዓመታት አለፉ፡፡ አድዋና ማይጨው ቦታ እንጂ ሥፍራ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ በኮርያ ጦርነት ጊዜ አሜሪካ 36574 ወታደሮች ሞተውባታል፡፡ የእነዚህ ሁሉ ወታደሮች ስም ዝርዝር በጦርነት መታሰቢያ ሙዝየሙ ላይ ተጽፏል፡፡ በጉራዕ፣ በጉንዲት፣ በዶጋሊ፣ በአድዋ፣ በማይጨው፣ በመተማ፣ በሶማልያ፣ በባድሜ የተሠዉት ወታደሮቻችን ለመሆኑ ስንት ናቸው? እነማንስ ናቸው? መቼ ነው ይፋዊ ዝርዝራቸው የሚነገረው? የሰው ዋጋ ተከፍሎ እንደዋዛ የምናልፈውስ እስከ መቼ ነው? የኛን ጦርነቶች ተዋጊዎች ዝርዝር ሁሉን ማወቅ ያስቸግር ይሆናል፡፡ የምናውቃቸውን ዘርዝረን ለረሳናቸው ደግሞ ‹ያልታወቀው ወታደር› የተሰኘውን ሐውልት ማቆም እንችላለን፡፡ ያለፉትን የሚረሳ ሰው ራሱ የሚዘነጋበትን መንገድ የሚጠርግ ነው ይባላል፡፡ መታሰቢያችን ከዘመናችን ማለፍ የሚችለው የቀደሙትን መታሰቢያ ከዘመናቸው ማሳለፍ ከቻልን ነው፡፡ 
የኮርያ የጦርነት ሙዝየም በጀግንነትና በኩራት የሚዘክራቸውን ኮርያውያንንና የየሀገሩን ባለውለታዎች ሳይ የሀገሬ ጀግኖች ያሳዝኑኛል፡፡ ዋጋ በከፈሉባት ሀገር እነርሱን የሚያስታውስና ታሪካቸውን በየትውልዱ ሊቀርጽ የሚችል ክብራቸውንና ደረጃቸውን የጠበቀ መታሰቢያ አላገኙም፡፡ ምናልባትም የሚያዝነው መንፈሳቸው ይሆን ሀገሪቱን በየዘመናቱ አዙሪት ላይ የሚጥላት?
ምንጭ :- ከዳንኤል ክብረት

 

Advertisement