መልካምነት እድሜ እንደሚጨምር አንድ ጥናት አስታወቀ

                             

መልካምነት የሚመሰገን ተግባር ብቻ ሳይሆን የመልካም አድራጊውን ሰው እድሜ እንዲጨምር ሊያደርግ እንደሚችል ኢቮሉሽን ኤንድ ሂውማን ቢሄቪየር በተባለ የሳይንስ መጽሔት ላይ የወጣ ጥናት ውጤት ይፋ አድርጓል፡፡

እንደ ጥናቱ ግኝት ከሆነ ቢያንስ አልፎ አልፎ ለሰዎች የሚራሩና ድጋፍ የሚያደርጉ ሰዎች በመልካምነታቸው የሚያገኙት ምርቃት ሰምሮላቸውን ሳይሆን አይቀርም በጎ ተግባር ከማያከናውኑ ይልቅ እድሚያቸው እንደሚልቅ ነው የተነገረው፡፡       

ጥንቱ የተካሄደው እድሜያቸው ከ70 እስከ 103 የእድሜ ክልል ባሉ 500 አረጋዊያን ላይ ነው ተብሏል፡፡

በጥናቱ መሠረት አያት የሆኑ አረጋዊያን አልፎ አልፎ የልጅ ልጃቸውን ሲንከባከቡ እንደዚሁም ለልጆች እንክብካቤ የማያደርጉ ግን ደግሞ በማህበራዊ መስተጋብራቸው በበጎ ተግባር የተሰማሩ ሰዎች በጥናቱ ተካተዋል፡፡

በጥናቱ የተካፈሉት ሰዎችም ለ20 ዓመታት በዘርፉ ተመራማሪዎች ክትትል ሲደረግባቸው የቆየ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

ለልጅ ልጆቻቸው እንክብካቤ የሚያደርጉ አያት አረጋዊያን እንዲሁም ልጆቻቸውን የሚደግፉ እማወራና አባወራዎች ጥናቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ለ10 ዓመታት በህይወት መቆየት ችለዋል ነው የተባለው፡፡

በአንፃሩ ይህን መሰሉን እንክብካቤና ሰናይ ተግባር ያልፈፀሙ ግማሽ ያህሉ የጥናቱ ተሳታፊዎች ጥንቱ ከተጀመረ ከ5 ዓመት በኋላ ህይወታቸው እንዳለፈ ተመልክቷል፡፡    

ከቤተሰባቸው ውጪ ለሌሎች ሰዎች ሰናይ ምግባር የሚያከውኑ ሰዎች ይህን ከማያደርጉ ሰዎች ይልቅ ህይወታቸው እንደጨመረ በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡

በመሆኑም በአቅሪያቢያቸው ለሚገኙ ሰዎች መልካም ተግባር የሰሩ ሰዎች ግማሾቹ ጥናቱ ከተጀመረ በኋላ ለ7 ዓመት በህይወት መቆየት ችለዋል፡፡

ይሁንና ይህን መሰሉን ተግባር ያላከናወኑ ሰዎች ደግሞ ጥናቱ ከተጀመረ በኋላ ለ4 ዓመት ብቻ ነበር በህይወት መቆየት የቻሉት፡፡

እንደ ጥናቱ ተመራማሪዎች ከሆነ በመልካምነትና በጤና በረከት ብቻ ሳይሆን በሰናይ ምግባርና በሞት ምጣኔ መካከል ግንኙነት እንዳለ ጠቅሰዋል፡፡ 

ጥናቱ ሌሎችን መርዳት እድሜ በእርግጠኝነት እንደሚጨምር ምንም ማረጋገጫ ባይሰጥም በጎ ምግባር የሚገኘው የመንፈስ እርካታ አሉታዊ ስሜቶችን ለማጥፋት እንደሚጠቅም የዘርፉ ተመራማሪዎች ያምናሉ፡፡  

በዘርፉ ላይ ተጨማሪ ጥናት ያስፈልጋል የሚሉት ተመራማሪዎቹ መልካምነትና ሰዎችን መርዳት ግን በአመዛኙ ለጤና መጠበቅና ለረጅም እድሜ ፍቱን መድሃኒት ነው ባይ ናቸው፡፡

ምንጭ፦ታይም 

Advertisement