እውነተኛ ፍቅርን የሚያጠናክሩ 5 ጠቃሚ ምክሮች

                    

1. በቂ የአብሮነት ጊዜን ማሳለፍ

በፍቅር የተቆራኘን ጥንድነት በመፍጠር ከጥብቅ ትዳር የተሳሰረን ጎጆ መቀየስ የአብዛኛዎቹ ጥንዶች የቀን ተሌት ህልምና ምኞት ነው፡፡ የጥንዶች ህልም እውን የሚሆነውና ምኞታቸው የሚሰምረው የጥንድነት መተሳሰሪያውን በበቂ ጊዜ በማጥበቅ ከሁለቱም ጫፍ መደገፍ ሲቻላቸው ነው፡፡ በዚህ የሁለትዮሽ አብይ ምሳሌ ከተጣመሩ ዘንድ የአብሮነትን ስሜት ለመዝራትና ጣፋጭ ፍሬውንም ለመቋደስ በቂ የአብሮነት ጊዜን መሰዋት ቀዳሚ ተግባራቸው መሆን እንዳለበት ይመክራል፡፡ በቂ ጊዜን መቸር መቻላቸው ለጥንድነታቸው ማዝገሚያ እርፍን፣ ለአብሮነት የአዝመራቸው ማሳን ስንክሳሩን መለያ (መውቂያ) አውድማውን እንዲሁም ለፍቅራቸው በቂ ስንቅንና ለትዳራቸው አስተማማኝ ጥረትን እንዲቋጥሩ ያግዛቸዋል፡፡
ስለዚህ ወረት ያላየውንና ጊዜ የማይሽረውን እውነተኛ ፍቅር ከሁለት በአንዱ ግንኙነት እጅ ለማስገባት ከሚሹ ሁሉ ወረት ያላየውንና ጊዜ የማይሽረውን በቂ ጊዜ ከምንም አስቀድመው (አስበልጠው) ከማንም ሰስተው (መስዋዕትነትን ከፍለው) ለጥንድነቱ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ከግንኙነቱ የወረት ሳንካዎች መሀል የአብሮነትን ምስጢርና የጋራ ድርሻን በመዘንጋት በተናጥል ለመወጣት መሞከር አንዱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ ደግሞ የግል ፍላጎትን ከመሙላትና የራስን ፍትወተ ስጋ ብቻ ከማድመጥና ከመከተል ላይ ያነጣጠረ በመሆኑ ለራስ ወዳድነት (Selfishness) ያጋልጣል፡፡ ከዚህም በላይ በጥምረት ለሚገፉን የጥንድነት አቀበትን ለብቻ ለመግፋትና ሸክሞቹንም ከአንድ ወገን ጫንቃ በመከመር እስከ የስነ ልቦና ችግሮች ድረስ ያደርሳል፡፡
በመሆኑም ከዚህ የፍቅር ጥምረት ጉዞ ላይ እያሉ ከመነሻው እስከ መድረሻው በመመካከርና ሀሳብ ለሀሳብ በመያያዝ (ልብ ለልብ በመተሳሰር) የልዩነት አቅጣጫዎችን ከመያዝ መውጣትና የተጣጣመና ቀላል ጉዞን በአብሮነት ጊዜ ውስጥ ማበጃጀት ይችላሉ፡፡

2. መራራውንም ጣፋጩንም ፅዋ በጥንድነት መጎንጨት

ጥንድነት በሁለትዮሽ የተገመደ የፍቅር አሀድ እንደመሆን አንድነቱ ጠቅልሎ የሚያስራቸውን ትሩፉቶች ብቻ ሳይሆን በአንድነቱ ተበትነው የሚፈቱ የእርካታ ችግሮችንም ማስተናገዱ አይቀሬ ነው፡፡ በተለይ ከዚህ የጥንድነት ጉዞ ጣልቃ የሚገቡና ፈታኝ መሰናክሎችን የሚጋርጡ ችግሮችን ጥንዶች ለየብቻቸው መጋፈጣቸው የአንድነቱ መፈተሻ ሆኖ በማገልገል ከአንደኛው ወገን የተለየ እክልን ይፈጥራሉ፡፡ እንግዲህ ይህን ጊዜ ነው የብዙ የስነ ልቦና ሐኪሞችን ቀልብ በገዛው የአብርሃም ማስሎ መርሆ የመመራትና አለመመራት ጉዳይ ትውስ የሚለን፡፡ የዚሁ እውቅ የስነ ልቦና ሐኪም መርህና አገላለፅ መሰረት በእንግሊዝኛው “Self-actual- evasion” በማለት ያስቀመጠውንና በአማርኛው ትርጉም ሲጠጋጋ ‹‹ከራስ በላይ ንፋስ፣ ከእኔ ወዲያ ለእኔ›› የመሳሰሉት የአኗኗር መፈክር ለጥንድነት የመለያያ መነሻ መንገድ ይሆናል፡፡ ይህን በእኔነት ተጀምሮ የእኔነት ማብቂያ የሌለውን የኑሮ ዘይቤ ወደ እኛነት ያልቀለበሱ ጥንዶች የጥንድነት ዕድሜ በባለሙያዎቹ ምክር ከአንዲት ጀምበር መድረሱ እንኳ አጠራጣሪ ነው፡፡ በጋራ የተነሳን ፅዋ እንደየአመጣጡና እንደየጣዕሙ በጋራ ለመጎንጨት እኔ የሚለውን ወደ እኛ የኑሮ ዘይቤና ማንነት ማምጣት ያዋጣል፡፡

3. በፍቅር አይን መተያየት

በተለይ የባለትዳሮችን የህይወት ጓዳ ድረስ የመዝለቅ፣ የትዳርን ሳንካዎች በመካፈል የመቆልመምን ዕድል ለበርካታ ዓመታት ለታደሉት አማካሪዎች የትዳር ህይወት የተለየ ትንታኔ አለው፡፡ የትዳር ህይወት በገሀዱ ዓለም የጓዳ መድረክ የሚከወን የመንትዮች ተውኔት ሌላ ምዕራፍ ሲሆን ከእነዚህ መንትዮች (ባልና ሚስት) የታዳሚነት ድርሻን ብቻ ጠቅልሎ መያዝ ብቻ ሳይሆን የሚጠበቀው የተዋናይም የታዳሚንም ድርሻ መያዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ይህ በባለሙያዎቹ አይን ሲታይ የራስንም የተጓዳኝንም የክወና ብቃት በትዳር ህይወት ውስጥ ለመፈተሽና ስለ አንደኛው አጋር ያለ አመለካከት ሁለቱንም ወገን ያስተያየና ያገናዘበ እንዲሆን ይረዳል፡፡
የተጓዳኝ የእርስ በርስ አመለካከት ሳንካን ሲያስከትል የሚያስተውለው በአብዛኛው ወደ ትዳር ከተገባ በኋላ ነው፡፡ በተለይ ‹‹ከመጋባታችን በፊት የነበረው ያ ሁሉ እንክብካቤ ያ ሁሉ ጉርሻ፤ ያ ሁሉ በሞቴ… ያ ሁሉ ቁልምጫ… ኧረ እጅና ጓንት ነበር የሚሉን… የዛሬን አያደርገውና ክንዶቹ ከቦታቸው ቢታጡ ቢታጡ ቀሪ አድራሻቸው ከወገቤ ነበር…›› የሚል የባለትዳር ሴቶች ስሞታ ከትዳር አማካሪዎቹ ጆሮ በተደጋጋሚ ለመድረስ አለመቦዘኑ እውነታውንና ችግሩን አጉልቶ ያሳያል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ልክ ከሁለቱም ወገን እንዳልታየ የዳኝነት ውጤት ‹‹ያብዬን ወደ እምዬ›› ላለመለጠፍ መጠንቀቅና የተጓዳኝ ድክመቶች (ግድፈቶች) አነጣጥሮ በማየት አቃቂር ከመፈለግ ‹‹በአንተ ትብስ…›› በጥላቻ አይን መተያየቱ ትዳርን ከማናጋት አይመለስም፡፡ በፍቅር አይን መተያየት በራስና በተጓዳኝ ውስጥ ያሉትን የፍቅር ችሮታዎች ትክክለኛ ገፅታ በቅጡና በትኩረት በመመልከት ለግድፈቶች የሚሰጥን ትኩረት በማቅለል እውነተኛ ፍቅርን በእውነተኛ ገፅታው ማቆም ይቻላል፡፡ ስለዚህ በፍቅር አይን በመተያየትና የሚያፈቃቅሩ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ጥንዶች እውነተኛን ፍቅር በአይናቸው ለማየት እንደሚችሉ ሊያውቁ ይገባል፡፡

4. የአመለካከት ልዩነቶችን ከአንድ ውስጥ ማውጣት

በተጓዳኞች ግንኙነት ውስጥ (በተለይ በባለትዳሮች) ሊከሰቱ የሚችሉ በርካታ የአንድነት ልዩነቶች በአመለካከት መለያየት አስታከው ከተፍ ማለታቸው አይቀርም፡፡ ከባለትዳሮች የትዳር ጎጆ እግር የጣለውንና ይህን መሰል ፅዋ እየተጎነጨ የደረሰ ወይም የደረሰበት ሁሉ የልዩነቶቹን ጣዕም በቅጡ ያውቃቸዋል፡፡
አንደኛው ወገን የሌላኛውን አመለካከት ለመቀየርና ለማሳመን የራሱን አመለካከት አክርሮ በመያዝ ‹‹እኔ ያልኩት ብቻ›› የሚልን አቋም ሲያራምድ ይስተዋላል፡፡ በተለይ ወረት ያላየውና እውነተኛን ፍቅር ጋልበው ከትዳሩ ዓለም መግባት ለሚሹት ጎጆን ከመቀለሳቸው አስቀድመው በመካከላቸው አንድነታቸውን የሚወስኑና ሁለትነታቸውን ብቻ የሚያመለክቱ በርካታ የህይወት ፍልስፍናዎች (እውነታዎች) በየግላቸው እንዲያዙ የሚያደርጉ አሉ፡፡
ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ የአመለካከት ልዩነቶች ከቀለሱት ጎጆ በር ሲያንኳኩ እንዳመጣጣቸው ለማስተናገድና ለመሸኘት የማይዳግታቸው፡፡ በተጨማሪም ፍቅርና ትዳር የመማማርና በመተራረም ሂደት የሚያሳድጉት እንደሆነ ቀስ በቀስ የሚረዱትና በሙሉ እርግጠኝነትና ተስፋ የዘላቂ የፍቅር ደጀን የሚሆናቸው፡፡

5. ለእውነተኛ ፍቅር አሸናፊነት መጣር

በመፈቃቀር የጥንድነትን ጉልበት መግለጥና የፍቅርን ፍቱን ኃይል መጋበዝ የሚቻለው ከሁለቱም ወገን በተውጣጣ የፍቅር ኃይል ነው፡፡ ጥንዶች ከየግላቸው የሚያዋጡት የፍቅር መስዋዕት (መፈቃቀር) ከአንድ መዋሉ ደግሞ ታላቅ የፍቅር ኃይልን በመፍጠር ለእውነተኛ ፍቅር ዘላለማዊ ጉልበትን ይቸራል፡፡
‹‹ከመቀበል ይልቅ መስጠትን ማስቀደም›› የፍቅር ቀዳሚ መርሆ እንደመሆኑ መጠን ፍቅርን ለመቀበል ፍቅር መስጠትን በማስቀደም ‹‹ከእኔነት›› በቀደመ ይልቁንም በ‹‹እኛነት›› የሚፀናውን እውነተኛ ፍቅር ከእጅ ማስገባቱ አይዳግትም፡፡
በትዳር ዓለም እያሉ ለዚህ ትዳር ዘለቄታ ይነስም ይብዛ ደፋ ቀና ማለት አይቀርም፤ በዚህን ወቅት ፍቅርን መስጠት ማስቀደሙ በፍቅር ህይወት የሚከሰቱ አለመግባባቶችን በፍቅር ኃይል በመግዛት ለመፍታት ፍቱን ጉልበትን ይሰጣል፡፡
የትዳር ህይወትን በአሸናፊነት ለመወጣት አንደኛ ወገን ሌላውን ለማሸነፍ (ለመግዛት) ከመሽቀዳደም ይልቅ በእውነተኛ ፍቅር (የመፈቃቀር) ጉልበት ለትዳሩ ለመገዛትና ለፍቅር አሸናፊነት ቅድሚያን መስጠቱ ይመረጣል፡፡ በእነዚህና መሰል የፍቅር ሀሳቦች ውስጥ መስዋዕት የሆኑለት ራሱ ፍቅር ነገ እነሱን መልሶ በፍቅር ይጠግናቸውና ፍቅር በፍቅር ያደርጋቸዋል፡፡ የፍቅር ሰዎችም ሆነን እንደ ምሳሌ የምንነሳ ያደርገናል፡፡ ለተጋቢዎችም ለአዲስ ተፈቃቃሪዎችም መልካም ፍቅር ይሁንላችሁ፡፡

ምንጭ :- ጤናዳም

Advertisement