የብዝሃ- ሕይወት ስብጥር ጥናት

                                            

በሸዋዬ ለገሠ እና አዜብ ታደሰ

ኢትዮጵያ በብዝሃ ህይወት ስብጥር በተፈጥሮ የታደለች ሀገር መሆኗን ተመራማሪዎች ይናገራሉ። በሀገሪቱና በዉጭ ሳይንቲስቶች ትብብርም በእጽዋቱ ዘርፍ ሰፋ ያለ ጥናት ተካሂዷል፤ አሁንም እየተካሄደ ነዉ። የተገኙ የጥናት ዉጤቶችን መሠረት ያደረገ የጥበቃ ሥራ መሠራት እንደሚኖርበትም ተመራማሪዎቹ ያሳስባሉ።

ላለፉት 38 ዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በእጽዋት ጥናት እና ምርምር ላይ ጊዜያቸዉን አሳልፈዋል። አሁንም በዚሁ መስክ ምርምራቸዉን ቀጥለዋል። አብዛኛዉን የዕድሜ ዘመናቸዉን በእጽዋት ምርምር ያሳለፉት ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰዉ፤ የጎርጎሪዮሳዊ 2016 ዓ,ምን የብሪታኒያዉ የሮያል ቦታኒክ ጋርደን ዓለም አቀፉን የኪዉ ሽልማት ለማግኘት በቅተዋል። ኩዉ ገልድ የተሰኘዉ ማኅበር በጎርጎሪዮሳዊዉ 1893ዓ,ም የተመሠረተ ሲሆን፤ ዋና ዓላማዉ የምድራችንን እጽዋት ዝርያ ማጥናት፣ መከታተል እና መጠበቅ ላይ ያነጣጠረ ነዉ። ለዚህም በዘርፉ የሚደረገዉን ጥናት ይደግፋል ያበረታታል።
እሳቸዉ እንደሚሉት ከጎርጎሪዮሳዊዉ 1950ዎቹ እና ከዚያ በኋላ የኢትዮጵያን ብዝሃህይወት የሚመለከቱ ጥናቶች አልነበሩም። የኢትዮጵያን የብዝሃህይወት መረጃ ለማሰባሰብ ፕሮፌሰር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር የጀመሩትን ፕሮፌሰር ሰብስቤ ከባልደረቦቻቸዉ ጋር ተረክበዉ ቀጥለዉበት ሥራዉን ማጠናቀቃቸዉንም ያስረዳሉ።  30 ዓመት በፈጀ  በዚህ ፕሮጀክትም ከኢትዮጵያዉያኑ በተጨማሪ ከ17 ሃገራት የተዉጣጡ ከ119 ሳይንቲስቶች በላይ መሳተፋቸዉንም ይገልጻሉ። የእጽዋቱን ምንነት ለማወቅ ስነምህዳሩን ማጥናት እንደሚያስፈልግ የሚናገሩት ተመራማሪ ካለፉት አምስት እና አራት ዓመታት በፊት ጀምሮም የኢትዮጵያን የስነምህዳር እጽዋት ሽፋን የሚያመለክት ዳጎስ ያለ የጥናት መጽሐፍ መዘጋጀቱንም አብራርተዋል። እንዲህ ያሉ ጥናቶች በመካሄዳቸዉም በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የሚገኙ 6,000 እጽዋት እጽዋቱ የት እንደሚገኙ ምን እንደሚመስሉ እና የመሳሰሉት አስፈላጊ ዝርዝር መረጃዎች፤ አሉ። ከእነዚህ ዉስጥም 600ዎቹ ኢትዮጵያ ዉስጥ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ እፅዋት መሆናቸዉን ፕሮፌሰር ሰብስቤ ገልጸዉልናል።ኢትዮጵያ የብዝሃ ሕይወት ቋት ናት የሚሉት ፕሮፌሰር ሰብስቤ የብዝሃ ህይወቱ መገኛ የሆነዉ የሀገሪቱ ደን እየተመናመ በመሄዱ ያላትን ሀብት በአግባቡ እንዳልተጠቀመችም ይናገራሉ።

ዋና ሥራቸዉና ትኩረታቸዉ ምርምሩና ግኝቱ ላይ መሆኑን የሚናገሩት የእጽዋት ምርምር ባለሙያዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ብቻ እንደሚገኙ የታወቀዉ ብርቅዬ የሆኑት እጽዋት ዝርያ እንዳይጠፋ ጥንቃቄ የማድረጉ ሥራ በቅንጅትና በጋራ መከናወን እንዳለበት ሳያሳስቡ አላለፉም።

ከጥናትና ምርምሩ ዉጤት ኅብረተሰቡ መረጃዎች እንዲያገኝም በተለያዩ እጽዋት ላይ የተካሄዱ ጥናት እና ምርምሮች ታትመዉ በየዩኒቨርሲቲዎቹ እንዲሰራጩ፤ እንዲሁም ጥናቶቹን ለማየት ለሚፈልጉ እንዲዳረሱም ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ከባለሙያዉ ለመረዳት ተችሏል።የእጽዋት ሳይንስ ተመራማሪዉ ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰዉ እንደገለጹልን አንዴ የኢትዮጵያ የእጽዋት ዝርያ በሙሉ ከተጻፈ በኋላ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በክልላቸዉ ያለዉን የእጽዋት ዝርያ መጻፍ ይችላሉ። እንዲህ ማድረግ ሲቻል ደግሞ መረጃዉ ለኅብረተሰቡ የተሻለ ቅርበት ይኖረዋል ብለዉም ያምናሉ። የብዝሃ ሕይወት ቋት ያሏት ሀገር ኢትዮጵያም በዩኒቨርሲቲዉ ከሚከናወነዉ ምርምር በተጓዳኝ ሀብቷን የምትጠብቅበትን ስልት ማጠናከር እንደሚገባም ሳይመክሩ አላለፉም።

ምንጭ :- DW

 

Advertisement