የዘመን መለወጫ በዓል ስያሜዎች

   

ይህ በዓል “የዘመን መለወጫ”፤ “አዲስ ዓመት” ከሚሉት በተጨማሪ ሌሎች ስሞችም አሉት፡፡

 ሀ. ቅዱስ ዮሐንስ

ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ተብሎ ከጌታችን ስብከት አስቀድሞ እንደሚመጣና ጥርጊያውን እንደሚያዘጋጅ በነቢዩ ኢሳይያስ ተነግሮለት ነበር /ኢሳ.40.3/፡፡ በዚህም መሠረት በዘመነ ብሉይ መጨረሻና በዘመነ ሐዲስ መጀመሪያ ተነስቶ «መንግሥት ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ» «እነሆ የዓለሙን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ» በማለት ስለ ጌታችን አዳኝነት መስክሯል፤ሕዝቡን ስለ ኃጢአታቸው እየገሰፁ ንስሐ እንዲገቡ አድርጓል፡፡ ጌታችንንም በዮርዳኖስ ወንዝ አጥምቋል፡፡

የቅዱስ ዮሐንስ ዕረፍት/ምትረት ርእስ/ የሚታሰበው መስከረም ሁለት ቀን ቢሆንም እንኳን ተግባሩ በዘመነ ወንጌልና በዘመነ ሐዲስ መካከል የነበረ መሸጋገሪያ በመሆኑ የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ መታሰቢያ በዓል የብሉይ ኪዳን ምሳሌ ከሚሆነው ካለፈው ዓመት የሐዲስ ኪዳን ምሳሌ ወደሚሆነው አዲሱ ዓመት መሸጋገሪያ በሆነው በመስከረም አንድ ቀን እንዲከበር፤ በዓሉም በእርሱ ስም እንዲሰየም አባቶ ወስነዋል፡፡

ለ. ርእሰ ዓውደ ዐመት

ዓውድ ማለት ዙሪያ፣ ክብ፣ ክስተቶች አንድ ጊዜ ከተከሰቱ በኋላ ደግመው የሚመጡበት ጊዜ ማለት መሆኑን ተመልክተናል፡፡ ስለዚህ ዓውደ ዓመት ማለት ዓመቱ አንድ ጊዜ ከተጀመረ በኋላ ሁለተኛ ዓመት እስኪጀመር ያለው ጊዜ ማለት ነው፡፡ ዓመትን መቁጠር ከየትኛውም ወር እና ቀን መጀመር ይቻላል፡፡ኅዳር 13 ብንጀምር አንድ ዓውደ ዓመት ማለት እስከሚቀጥለው ኅዳር 12 ቀን ያለው ጊዜ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን መደበኛው ዓውደ ዓመት የሚጀምረው መስከረም አንድ ቀን ነው፡፡ ይህ ቀን ርእሰ ዓውደ ዓመት የተባለውም «የሁሉም ዓውደ ዓመት መጀመሪያዎች ቁንጮ ነው» ለማለት ነው፡፡

ሐ. ዕንቁጣጣሽ

ሐጎስ ዘማርያም ለምለም በቀለን ለመጀመሪያ ዲግሪ ማሟያ ያቀረበችውን ጽሑፍና ሌሎች የቃል ማስረጃዎችን ጠቅሶ በሐመር መጽሔት የ1997 ዓ.ም መስከረም/ ጥቅምት ዕትም ላይ በቀረበው ጽሑፍ «ዕንቁጣጣሽ» ለሚለው የዚህ ስያሜ ሁለት ዋና ዋና መነሻዎችን እንዳሉት ገልጿል፡፡

 

  1. ዕንቁጣጣሽ የሚለው ቃል ሁለት ቃላት ካሉት ጥምር ቃል የተገኘ ነው፡፡ ዕንቁ እና ጣጣሽ ከሚሉ ዕንቁ የከበረ ዋናው ውድ የሆነ አብረቅራቂ ድንጋይ ነው፡፡ ጣጣሽ የሚለው ቃል ፃዕ ፃዕ ከሚለው የግእዙ ቃል የተወረሰ ሲሆን ትርጉሙ ግብር፣ ጣጣ፣ ገጸ በረከት፣ ማለት ነው፡፡ለምሳሌ በሸዋ አካባቢ ግብር አለብኝ ሲል «ጣጣ አለብኝ» ይላል፡፡ይህ ስያሜ ለበዓሉ የተሰጠው ከንግሥተ ሳበ /ንግሥት ማክዳ/ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ንግሥተ ሳባ ንጉሥ ሰሎሞንን ለመጎብኘት ሔዳ ሳለ የጸነሰችውንቀዳማዊ ምኒልክን በወለደች ጊዜ ሕዝቡ ንጉሥ ተወለደ ብሎ እልል እያሉ «አበባ እንቁ ጣጣሽ» እያለ ገጸ በረከት ለንግሥቲቱ አበረከቱ፡፡ያ የዘመን መለወጫ በዓልም ልጃገረዶች የአበባ ገጸ በረከት የሚያቀርቡበት ስለሆነ ዕንቁጣጣሽ ተባለ፡፡
  2. ዕንቁጣጣሽ ግጫ ማለት ነው፤ ግጫ ደግሞ የሣር ዓይነት ነው፡፡የአበባ፣ የእርጥብ ስጦታ መስጠት የተጀመረው በኖኅ ዘመን ነው፡፡ ኖኅ የጥፋት ውኃ በጎደለ ጊዜ መጉደሉን ለማረጋገጥ ርግብን ልኳት የወይራ ቅጠል አምጥታለች ይህ የሆነበት ወቅት የመስከረም ወር በመሆኑ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የዘመን መለወጫ ሆነ፡፡በርግቧ አምሳልም ልጃገረዶች የተለያየ ዓይነት ሣርና አበባ በመያዝና በማደል በዓሉን ያከብራሉ፡፡ በሣሩ ስምም በዓሉ ዕንቁጣጣሽ ተባለ፡፡
 

Advertisement