ባቡር፣ መንገድና የሰው ጠባይ

   

ከአዳም ረታ

ተመርቆ የቆየው የባቡር መንገድ ስራ የጀመረ ጊዜ “ከተማችን ዘነጠች” ተባለ። “ዓለሟን አየች” ተባለ። በየልቡ “አሁን ደመቅሽ አዲሳባዬ” ተዘፈነላት። ሰው ደስታውን በተለያየ መንገድ ገለጸ። የትናንት መልካም ታሪኮችን ስለዛሬ መስዋዕት ያቀረቡ አሽቋላጮችም ነበሩ። አንዳንድ የአዲስ አበባ ኗሪዎች እጅጉን ተመጻደቁ። በነዋሪው ግብርና፣ ነገ ላቡን ጠብ አርጎ በሚከፍለው (አልያም ሞልቶ ከተረፈው ተፈጥሯዊ ሀብት በዓይነት በሚከፈል) ብድር መሰራቱን የማያውቁ ይመስል ብሽሽቅ ጀመሩ። የስልጣኔ አልፋ መሆኑን አወሩ። “የ24 ዓመቱ ልፋት አፈራ” አሉ።

ለባቡር መንገድ ስራ ጫካ የተገባ ይመስል “የታጋዮች ደም ፍሬ እያፈራ ነው።” ተባለ። ሬድዮና ቴሌቪዥኑ ሌላ ስራውን ትቶ፥ ከሞላ ጎደል ባቡሩን ማውራት ጀመረ። ከባቡሩ በሚተርፈው ጊዜ ባለጊዜውን “ሞላ” ያቀነቅናል። ሰልፌዎች በየሰዉ ግድግዳ ተለጣጠፉ። ወሬው ባቡርና ባቡር ብቻ ሆነ። ጋዜጠኞቹ ከምን ጊዜውም በላይ መበጥረቅ ጀመሩ። አንዱ “ይሄን ታሪካዊ ትኬት አልበም ውስጥ አስቀምጬዋለሁ” ሲል ገረመኝ። ለወሬ ሲቸኩል፥ “ትልቅ ዋጋ ያለውን አረንጓዴ ትኬት ቆርጬ ረዥሙን መንገድ ነው የሄድኩት።” አለ። (ትልቅ ዋጋ ያለው ትኬት ቀዩ ነው እንጂ አረንጓዴው አይደለም።)

ወዲህ ከፒያሳ ተነስቶ ቃሊቲ፣ ወዲያ ደግሞ ከጦር ኃይሎች ተነስቶ ሀያት የሚዘልቁ ሁለት መንገዶች ተዘረጉና ከተማችን ቄንጠኛ ሆነች ተባለ። ሰዎች ደግሞ መውረጃቸው ጋር ሲደርሱ ወደጉዳያቸው ቶሎ እንደመሄድ ወገባቸውን ይዘው እዚያው ቆመው ወሬያቸውን ሲሰልቁ ይውላሉ። የባቡሩ መንገድ ሊሰራ ሲቆፈርና በልምምድ ወቅት፣ ከብበው ይመለከቱ ከነበረው በላይ ሰዎች የባቡሩን ማለፍ ቆመው ይመለከታሉ። ያወራሉ። ምን እንደሚያወሩ ግን አይገባኝም ነበር። ፖሊሶችና ትራፊኮች የባቡር ጣቢያዎች ላይ ፈሰሱ። በቻይኖች እየተዘወረች ባቡሯ ብቅ ስትል (በየ6 ደቂቃው ነው ተብሏል) ሰዉን ያዋክቡታል። ከድንዛዜው የተነሳ ሀዲዱ ላይ ሲሰጣ፣ ተገርፎ የሚወጣም ነበር። (ሲያንሰው ነው።)

እንዳያያዛቸው፥ የባቡሩ መንገድ ስር፣ እና ጎንና ጎን፣ አንድ ቀን እሳት አንድደው፣ ጀበና ጥደው ቡና ሳይጠጡም አይቀር። ዳስ ጥለው ጠላ ሳያንዶቆድቁም አይቀር። የእድር ስብሰባዎችም እዚያ ሳይካሄዱም አይቀር። መጀመሪያ ሰሞንማ ባቡሩን ለማየት ከቤት ተቀሳቅሰው የሚወጡ ነበሩ። እንደ ቤተ አምልኮ ሊሳለሙት ይመስል ነጠላ ጎትተው ዋናው መንገድ ላይ የሚውሉ ጎልማሶች ተበራከቱ። ጎረምሶችና ኮረዶች ደግሞ መቀጣጠሪያቸውን የባቡሩ መንገድ ያለበትን አቅጣጫ ብቻ አድርገውታል።

በየስልኩ “ሃሎ! እሺ… አልቆይም ኧረ። ባቡሯን ይዤ ነው የምመጣው።”፣ “ውይ ባቡሯ አመለጠችኝ። በቃ ቀጣይዋን እይዛለሁ።”፣ “ባቡር አትይዥም? አቦሉ ላይ ድረሺበት…”፣ “ለትንሽ አረንጓዴዋ ትኬት አለቀችብኝ። በቀይዋ መጥቼ አቆራርጣለሁ። አልቆይም…” የሚሉ የስልክ ወሬዎች መሰማት ጀመሩ። “ችግር ያቅልል ተብሎ ችግር ሆነ እኮ። ታያለህ መንገዱን እንደዘጋጋው?” የሚሉ አሽከርካሪዎች በዙ። ።

የባቡሩ መጫኛና ማውረጃ ቦታዎች ሁልጊዜ ትርምስ ሆነ። መንገድ መዘጋጋት ጀመረ። በተለይ ባቡሩ ዝቅ ብሎ፣ ከመኪና ጋር እየተጠባበቀ በሚያልፍበት ቦታዎች ላይ የትራፊኩ ጭንቅንቅ በዛ። ታቦት እንደሚሸኙ ሁሉ ተሻጋሪዎች ተከትረው ቆመው ይጠብቃሉ። የመርካቶ በራፎች ትርምስ በዛባቸው። ወትሮም ግር ብለው ሲወጡና ሲገቡ ቀብር የሚሄዱ የሚመስሉት የመርካቶ ሰፈር ነዋሪዎች መውጫና መግቢያ ላይ፥ አስከሬን ቆመው የሚያሳልፉ ይመስል… አልቃሽ ያዙኝ ልቀቁኝ ብላ ስትፈጠፈጥ ቆመው እስክትነሳ ይጠብቋት ይመስል…መውጫና መግቢያው ላይ መገደብ ጀመሩ። ትራፊክና ፖሊሶች ላይም ጭንቅ ሆነ። መጀመሪያ ሰሞን፥ ሰዉ ጉዳይ ሳይኖረውም ለሙከራ ይሳፈር ነበር። “እስኪ ሽርሽር እንውጣ” ይላሉ። ለሙከራ የሚሳፈሩት ሰዎች ፊት የመገረም ፈገግታ ፊታቸውን ሞልቶት ይታያል።

ትንሽ ከርሞ ከተማዋ በዚህ ባቡር ከዘነጠች በኋላ እናቴ አንድ ሀሳብ ተከሰተላት። ካልጠፋ ነገር ባቡሩ ጣቢያ ጋር ቆሎ የማዞር ሀሳብ ተከሰተላት። መንገድ ሲሄዱ መኪና ተበላሽቶ ወርደው የሚተራመሱ ሰዎችን ሲያይ፥ “እዚህ ጋር ሻይ ቤት መክፈት ነበር” እንዳለው ስራ ፈጣሪ ጉራጌ እናቴም የስራ ሀሳብ ተከሰተላት። በቆሎ ጀምረነው፣ የሰዉን ፍላጎት እያየንና እንደ ወቅቱ ድንችና በቆሎም እንጨምራለን አለች። በፕላስቲክ የተለበጠ “ሞባይል ካርድ አለ” የሚል ወረቀት አንገቴ ላይ አንጠልጥዬ፣ ማልጄ ቆሎዬን ይዤ እንድወጣ ተፈረደብኝ።

ባቡሩ እንቅልፌን ቀማኝ። ባቡሩ ልጅነቴ ላይ ተደራደረ። እንደፈረደብኝ ባቡር ለሚጠብቁ ሰዎች ቆሎዬን መስፈር ጀመርኩ። እንደ ስራ ሳይሆን እንደቅጣት ስለምቆጥረው በደስታ አድርጌው አላውቅም። ባቡሯ እንዳታመልጣቸው ሲዋከቡ መልስ ጥለው የሚሄዱ ሰዎች ሲያጋጥሙኝ ደስ ይለኝ ጀመር። እንደዛ ሲሆን “ስትመጣ ትከፍላለህ… ቅመሳት” እያልኩ መቀናጣትና ገበያተኛ ማማለል ይቃጣኛል።

አንዳንዴ ደግሞ የፋጤ እድል ይገጥመኛል። ማንጎ ሸጣለት “ሽልንጌን” እያለች የጮኸችው የሀረሯ ፋጡማ ትዝ ትለኛለች። አንዳንዱ ቆሎዬን ሰፍሬለት ሳይከፍለኝ ባቡሯ ውስጥ ይገባል። እንዲህ ሆነ ስራዬ። ባቡሯ በመጣች ቅጽበት እንደ ሀይለኛ ዝናብ ሿ ይልና፣ ወዲያው ቀጥ ብሎ ያባራል። ሰፌዴን ይዤ እንደነገሩ ትከሻዬ ላይ ጣል አድርጌው እወጣና ባቡር መንገዱ አካባቢ በፀጥታ ገዢ እቃርማለሁ። ባይኖቼ እለማመጣለሁ።

ባቡር ጠባቂው “መጣች መጣች” ይባላልና አንገት ሁሉ ሰግጎ ባይኑ አቀባበል ያደርግላታል። እሪ ይባላል፣ ይጮሃል፣ ይገፋፋል። ጨዋ የሚመስሉ ሴቶች እንኳን ቀሚሳቸውን ሰብስበው ይሯሯጣሉ። ቆሎዬን ሽጬ እቤት ከተመለስኩ በኋላ ሌላ ቆሎ ከሌለ፣ የሞባይል ካርዶቼን ይዤ ሰፌዱን አስቀምጬ እወጣለሁ። ከዚያ ለተባራሪ ፈላጊ ሞባይል ካርድ እየሸጡ ወሬ መስማት ነው።

ባቡሩ መጀመሩ አንድ ትልቅ የወሬ ለውጥ አመጣ። ሕዝቡ ለታክሲ መጋፋቱን በባቡር መጋፋት ተካው። የሚሄድበት መንገድ አጭር የታክሲ ወይም የእግር መንገድ ቢሆን እንኳን፥ እንደምንም ብሎ ባቡሩ በሚሄድበት አቅጣጫ ሄዶ፣ በታክሲ ማቆራረጥ ጀመረ። ባቡሯን ለመጠቀም ቀደም ብሎ እየወጣ ራሱ ላይ መከራ ከመረ። ወሬው በየቦታው በየቤቱ በየቅያሱ ስለባቡርና በባቡር ስለመሄድ ሆነ። ቃሊቲና ቂሊንጦ ያሉ እስረኞችን የሚጠይቅና መንጃ ፍቃድ የሚያወጣው ሰው በዛ። ባቡሯን ቃሊቲ ድረስ ለመጠቀም ብሎ ወጥቶ ደብረ ዘይት ሄዶ የሚዝናናውም ሰው ጨመረ።

“ፍጥነቱ ደስ ሲል። ደግሞ የሚሄድም አይመስልም… ”

“መንገጫገጭ የለ… ታክሲው እኮ ሲንጠን እንዴት ገድሎን ነበር?”

“አንቺ ባቡሩን ሞከርሽው? ወደ ሀያት ስትሄጂበት ደግሞ ከቃሊቲው ይለያል።” ትንታኔዎች ተደሰኮሩ።

“ትላንት ለቅሶ ሄጄ… እንዴት ፈጥኜ መጣሁ መሰለሽ።” (ሰው ሲሞቱና ትልልቅ ጉዳዮቹ እንዳያልፉት ባቡሩ መንገድ ተከትሎ ያሉ ዘመዶቹ ጋር ዝምድናውን አጠበቀ።)

“ደግሞ ከታክሲው ሲናጸር ዋጋው መርከሱ… ታክሲዎቹማ ሲበዘብዙን ኖሩ እኮ።”

“ኧረ የረዳቶቹን ስድብ መጠጣቱና የጣሉትን ቂጥ ማየት መቅረቱስ”

“’ድመት መንኩሳ ዐመሏን አትረሳ’ …አሁን ምንድን ነው መስገብገብ። ሆዱ እኮ ሰፊ ነው። ሁላችንንም ይችለናል። ኧረ ተዉ ቻይኖቹም ይታዘቡናል…”

“ኧረ ደቂቃው እንዳይሞላብሽ ፍጠኚና ውጪ”

“ለትንሽ ጥሎኝ ሊፈረጥጥ። ሀዲዱ ላይ መዳመጤ ነበር…ብቻ ብረቱን ይዤ ተረፍኩ።”

“ባቡር ላይ እያስቸገረኝ ነበር። ስልኬን ወስዶ…”

“እንዴ ባለቤቴ እኮ ባቡሯ እንዳታልፈው ስለሚጣደፍ ማምሸቱም ቆሟል። ይኸው በጊዜ፣ መጥቶ ስንላፋ ነው የምናመሸው ስልሽ…”

ጨዋታው ባቡርና ባቡር መንገድ ሆነ።

ባቡር ባቡር የሚሉ ዘፈኖች፣ የድሮ የዘፈን ክሮች እየተራገፉ ወጡ። አዳዲስ ግጥምና ዜማዎችም ተቀመሩ። ችኮላው አላደርስ ያላቸው የቀድሞ ዘፈኖችን ግጥሞች አድሰው ሬድዮዎቹን አጨናነቁ።

ባለጋሪው ባለጋሪው፣
ቶሎ ቶሎ ንዳው…

የሚለው ዘፈን ግጥም ተቀይሮ…

ባለባቡሩ ባለባቡሩ፣
ሸገር ሆኗል ሀገሩ!

ተሳፋሪ ሁሉ ባለ ጉዳይ ነው
ታክሲና አቶቢሱን አሻግሮ ሚያየው
የሞላ የሞላ ባለና በፊቴ
ባሳፈረኝና እፎይ ባለ ስሜቴ፤
እፎይ ባለ ስሜቴ፤

ተብሎ በየኤፍ ኤሙ ተሰማ።

በባቡር በፍቅር መንገድ ላይ በባቡር
በባቡር በመውደድ መንገድ ላይ በባቡር
መጓዝስ ካልቀረ ካንቺ ጋር ነበር

የሚለው ሙዚቃ እንዳንዲስ መጠባበሻ ሆነ።

በባቡሩ መንገድ የቆምኩት አሁን
ስንቱን አሳልፌ ልዘልቀው ይሆን?

የሚለው የሜሪ አርምዴ ዘፈን ከነክራሩ ከተሰቀለበት ወረደ።

በየታክሲው ጭቅጭቁ፣ ማስፈራራቱና ዛቻው በዛ።

“ኤጭ አትጨማለቅ እንግዲህ! ባቡር እኮ…” እያሉ የሚያስፈራሩ፣ “’እጸድቅ ብዬ ባዝላት…’ አንተ በባቡር መሄድ አቅቶኝ አይደለም።” እያሉ የሚመጻደቁ፣ “እንደውም ተወው ባቡሯ ብቅ አለች” ብለው የሚያኮርፉ ተሳፋሪዎች በረከቱ።

“ታክሲ ጥንቡን ጣለ” ተባለ።

ስጋቶችም አልጠፉም።

“መብራት ቢጠፋስ?”፣ “ደግሞ ሲዘንብ ቢነዝረኝስ?”፣ “ይሄ ደንባዛ ቻይና ቢያስነጥሰውና ዐይኑ ጭራሽ ድርግም ቢልስ?” የሚሉና ሌሎች የፍርሃት ወሬዎች በሹክሹክታና በየሰዉ ልብ ውስጥ ይብላሉ ጀመረ።

“ባቡር ጣቢያው ጋር ጠብቂኝ” “ምስጢራዊ የባቡር ጉዞዎች” “መሀልየ መሀልይ ዘባቡር” “የባቡሩ ጉዶች” “ባቡር ላይ ያየሁት ወንድ የወሰደው ልቤ” “ባቡር ተሳፍሬ” “የዘገየው ባቡር” “ከባቡር አደጋ ለመትረፍ የሚያስችሉ 8 ነጥቦች” “ባቡርን ወደ ቢዝነስ የመቀየር ጥበብ” “የባቡር ኬሚስትሪ” “ባቡሩ” “ከባቡር የወጣች ነፍስ” “ባቡር መንገዱ ዙሪያ ያሉ የወሲብ ሕይወቶች”…የሚሉ የተለያዩ ከተፋ መፅሐፍትና ፊልሞች በዙ። ሙዚቃዎችም ባይነት ባይነቱ ሆኑ። ገጣሚያንም ወገባቸውን ቋጥረው ስለባቡር ተቀኙ። ናፍቆትና ጥበቃ በባቡር ተሰማመሩ።

“የከሸፈው የአሸባሪዎች ሴራ በባቡሩ መንገድ ላይ”፣ “እንደ ባቡራችን ፈጣኑ ኢኮኖሚያችን”፣ “ባቡር ላይ በሻዕቢያ ተላላኪ ፀረ ሰላም ኃይሎች የተቀነባበረው ፍንዳታ ምስጢር ተጋለጠ”፣ “አቶ አንዳርጋቸው እንደ ኤክስፕረስ መንገዱ የባቡሩንም ጎበኙት። ይህኛው የባቡር ጉዞዬ ከእስከዛሬው ሁሉ ለየት ያለ ነው አሉ።” እና የመሳሰሉ ዶክመንተሪዎችና የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ርዕሶች በብዛት መታየት ጀመሩ።

እኔ ግን ኑሮ ባቡር ላይ ተጭኜ ቆሎ እሰፍራለሁ እንጂ እስከዛሬ ባቡር ተሳፍሬ አላውቅም። ባቡሩ ሆዴን እያሰብኩ ባቡር ተሳፋሪን አሳድዳለሁ። በቆሎና ስለቆሎ ያየሁት ጉድ ይበዛል። ሳድግ ግን “ባቡር መንገድ ላይ ያሳለፍኩት ልጅነቴና ትዝብቶቼ” ወይም “ባቡር መንገድና የሰው ልጅ ጠባይ” ወይም “ባቡርና ሕይወት” ወይም “ባቡር ጣቢያ ላይ የተረሳው የትንሹ ልጅ ሕይወት” የሚል መጽሐፍ ብጽፍ ደስ ይለኝ ነበር። ትምህርት ቤት አልሄድኩም እንጂ መጻፍ ብለምድና መጽሐፍ ብጽፍ ደስ ይለኝ ነበር።

‘ግን ሰው ከባቡር መሳፈርና ስለባቡር ማውራት ምን ጊዜ ተርፎት ያነብልኛል?’ ስል አስባለሁ።

ማስታወሻ
ይህንን የጻፍኩት የአዳም ረታ “ግራጫ ቃጭሎች” ላይ ገጽ፥ 127-128 ባለው “ቧንቧ፣ ልብስና የሰው ጠባይ” በሚል ንዑስ ርዕስ በተጻፈው ታሪክ መቆስቆስና ቅርጽ ነው። አንዳንድ አረፍተ ነገሮችንም በቀጥታ ከግራጫ ቃጭሎች ላይ ገልብጫለሁ።

 

 

 

 

 

Advertisement